Fana: At a Speed of Life!

ከማህፀን ውጭ እርግዝና

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከማህፀን ውጭ እርግዝና የሚባለው ጽንስ ከሚቀመጥበት የውስጠኛው የማህጸን ግድግዳ ውጭ ተጣብቆ ሲቀመጥ ነው።

ከ95 በመቶ በላይ ከማህፀን ውጭ እርግዝና በቦየ እንቁልጢ (fallopian tube) የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የሚፈጠር ሲሆን÷ ቀሪው ደግሞ በእንቁልጢ (ovary)፣ በማህፀን ጫፍ፣ በማህፀን ጠባሳ እና በሆድ ውስጥ ላይ ወዘተ ሊከሰት ይችላል።

ከማህጸን ውጭ እርግዝና የመፈጠር እድልን የሚጨምሩ ነገሮች ምንድን ናቸው?

የቦየ እንቁልጢ ኦፕሬሽን፣ ከዚህ በፊት የተፈጠረ የማህፀን ውጭ እርግዝና፣ ቦየ እንቁልጢን የሚያጠቃ ማንኛውም ችግር፣ በማህጸን ውስጥ የሚቀመጥ የወሊድ መከላከያ ዘዴ፣ በሰው ሰራሽ ዘዴ የሚፈጠር እርግዝና/ኢንቪትሮ ፈርቲላይዜሽን (IVF)፣ ሲጋራ ማጨስ ናቸው፡፡

እንዲሁም ከማህጸን ጫፍ በላይ ያሉ የሴት ልጅ የመራቢያ ክፍሎችን የሚያጠቃ ኢንፌክሽን ፣ መካንነት ፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን መጠቀም ከማህጸን ውጭ እርግዝና የመፈጠር እድልን የሚጨምሩ ነገሮች ናቸው፡፡

ከማህፀን ውጭ እርግዝና ምልክቶችስ ምንድናቸው?

ከማህጸን ውጭ እርግዝና ምልክቶች በብዛት የመጨረሻው የወር አበባ ጊዜ የመጀመርያ ቀን ከታየ ከ 6 እስከ 8 ሳምንታት ውስጥ ባሉ ጊዜያት መታየት እንደሚጀምር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዋና ዋና ምልክቶችም በታችኛው የሆድ ክፍል በአንድ በኩል የሚሰማ የሆድ ህመም ፣በከረቤዛ በኩል የሚወጣ የደም መፍሰስ (vaginal bleeding)፣የወር አበባ መቅረት ሲሆኑ አልፎ አልፎ እንደየበሽታው ደረጃ ራስ ማዞር፣ ብዥ ብዥ ማለት ፣ በትከሻ አካባቢ የሚሰማ ህመም እንዲሁም በጤነኛ እርግዝና ጊዜ የሚታዩ እንደ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ… ወዘተ የመሳሰሉ ምልክቶች ሊኖሩት ይችላል ።

ከማህጸን ውጭ እርግዝና እንዴት ይታከማል?

አካላዊ፣ የላቦራቶሪ እና አልትራሳውንድ ምርመራዎች ከተደረጉ እና ከማህጸን ውጭ እርግዝና መሆኑ ከተረጋገጠ የህመሙ ደረጃ እና የታካሚዋ የጤና ሁኔታ ታይቶ ህክምናው ይሰጣል ።

የሚሰጠው ህክምና እንደታካሚዋ የጤና ሁኔታ እና የህመሙ ደረጃ የሚለያይ ሲሆን÷ የህክምና አማራጮችም ፥የኦፕሬሽን (ቀዶ ጥገና)ህክምና ፣በመድሀኒት የሚደረግ ህክምና እና የክትትል ህክምና ናቸው ።

ከማህፀን ውጭ እርግዝና በደም መፍሰስ ምክንያት ለሚከሰት የእናቶች ሞት አንደኛው እና ዋነኛው ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.