Fana: At a Speed of Life!

የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ አሰራር መተግበር የሚያስችል የአምስት ዓመት የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በአፍሪካ ማዕቀፍ ሀገር አቀፍ የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታ እንዲያዘጋጁ ከመረጣቸው 12 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡

በዚህም መሰረት በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ደህንነቱ ባልተጠበቀ ምግብ የሚከሰተውን በሽታ ለመቀነስና ሞትን ለመከላከል የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡

በአፍሪካ ህብረት የገጠር ልማት ክፍል ሃላፊና የግብርናና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ተወካይ ዶክተር ጃኔት ኢደሜ እንዳሉት÷ በአፍሪካ በምግብ መመረዝ ምክንያት ለበሽታ የሚዳረጉ ሰዎችን ለመታደግ የምግብ ደህንነት ስትራቴጂ ወሳኝ ነው፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ እንዲፋጠን ከማገዝም ባለፈ አባል ሀገራት ከአፍሪካ የአፍላቶክሲን ቁጥጥር ህብረት ጋር እንዲሰሩ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታ ቀድማ በማዘጋጀት ለጉዳዩ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ጀምራለች ብለዋል፡፡

በመሆኑም ህብረቱ እንዲህ አይነት ጉዳዮችን በቁርጠኝነት ለሚተገብሩ ሀገራት የሚያደርገውን ድጋፍ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የምግብ ደህንነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሁሉም ጉዳይ በመሆኑ የተዘጋጀው ሀገር አቀፍ የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታ ትግበራ የሁሉንም የተቀናጀ ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የተቋማት ወጥነት ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ፤ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ከዘር ጀምሮ ለምግብነት እስከሚውሉበት ድረስ ባለው የእሴት ሰንሰለት ደህንነቱን መጠበቅ ይገባል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.