Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን በጋራ ለመከላከል ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ፖሊስ ተቋማት ሽብርተኝነትና ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን በጋራ ለመከላከል ተስማሙ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት ኃላፊ ኢንስፔክተር ጀነራል አቲም ማሮል የተመራ ከፍተኛ የፖሊስ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት ከዚህ ቀደም በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት በርካታ ድጋፎችን ማድረጉንና አሁን ላይም በሪፎርሙ የተፈጠሩ ስኬቶችንና ልምዶችን ለደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት እንደሚያጋራ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገልፀዋል።

ኢንስፔክተር ጀነራል አቲም ማሮል በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት የተለያዩ የትምህርት ዕድሎችን በመስጠት ወጣት የፖሊስ ኦፊሰሮችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝና ለወደፊትም ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት አፈጻጸም ላይ ተወያይተው በተለይ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ የሚስተዋለውን ሽብርተኝነት እና ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን በጋራ ለመከላከልና በትብብር አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል።

ይህን የሚያስፈጸም ቴክኒካል ቡድን በማቋቋም የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች በቅርቡ በጋምቤላ ተገናኝተው እንደሚወያዩ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

የልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዜጎች ተሳትፎ መረጃ መተግበሪያን በጎበኘበት ወቅት ጀነራል አቲም ማሮል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀመ እንደሚገኝ ኢንስፔክተር ተገንዝበናል ብለዋል።

በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያን በጎበኘበት ወቅት፥ ጠቅላይ መምሪያው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ የተጠርጣሪ ቃል መቀበያ ክፍሎችን አደራጅቶ ሪፎርሙን ተግባራዊ በማድረግ ሰብዓዊ መብትን ያከበረ፣ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የተከተለ የተጠርጣሪ አያያዝ መተግበሩን ኢንስፔክተር ጀነራሉ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.