Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን የሚመስል ሰራዊት ተገንብቷል – ጄኔራል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ግዳጅ የመፈፀም አቅምና ከፍተኛ ሀገራዊ ፍቅር ያለው፤ ኢትዮጵያን የሚወድና የሚመስል ሰራዊት ተገንብቷል ሲሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ፡፡

ጄኔራል አበባው የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጥኖ ላስመረቃቸው የበታች ሹም አመራሮች በወቅታዊ ተቋማዊ ሀገራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ ገለፃ አድርገዋል።

በገለፃቸውም÷ የኢትዮጵያን ትልቅነት የሚረዱ ታሪካዊ ጠላቶች በገንዘብ በቀጠሯቸው የውስጥ ተላላኪዎች ሀገር አፍራሽ አጀንዳ በመስጠት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ትንኮሳ ለመፈፀም ቢሞክሩም በጀግናው ሰራዊታችን መስዋዕትነት ክፉ ህልማቸው እንዳይሳካ ተደርጓል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የማይገባትን ጥቅም ጠይቃ አታውቅም ወደፊትም አትጠይቅም ያሉት ጄኔራል መኮንኑ÷ ብሄራዊ ጥቅሟን ከጥቃት የሚጠብቅ ሁለንተናዊ አቅም ያለው የመከላከያ ሰራዊት የመገንባት ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የሸኔ የሽብር ቡድንና የፅንፈኛው ኃይልን ወደ ስርዓት ለመመለስ በተደረገው ጥረትም ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በኃይል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሞከሩ ኃይሎች ህልም መምከኑን ገልጸው÷ ፅንፈኞች የቀራቸው ጉልበት በሚዲያ ላይ ህዝቡን ማሸበር ብቻ ነው ብለዋል፡፡

በንግግርና በተግባር መካከል ከፍተኛ ለውጥ መኖሩና በመሬት ላይ በተሰራው ውጤታማ ተግባር የፅንፈኞችንና የተከፉይ ፕሮፓጋንዲስቶች የሚዲያ ጫጫታን ማክሸፍ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

ከወረዳ ያለፈ ሐሳብና ህልም የሌላቸው የሸኔ ቡድንና የፅንፈኛው ኃይሎች በሚፈፅሙት ግፍ ከህዝቡ ተነጥለው እርስ በእርሳቸው እየተገዳደሉ እንደሚገኙ እና የሎጂስቲክ፣ የመረጃና የሰው ኃይል እጥረት እንዳጋጠማቸውም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን የማይሰጡትና ተበታትነው የሚገኙትን ትንንሽ ቋጠሮዎችን የማፅዳት ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በሰራዊታችንና በህዝቡ ጥረት በአብዛኛው ቦታዎች ላይ የመጣውን ሰላም ለማስቀጠል በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

ሰራዊቱ የሚለካው በአስተሳሰቡና በስነ-ልቦናው ጥንካሬ በመሆኑ÷ በብዙ ፈተናዎች በፅናት ያለፈ፣ ጠንካራ ወታደራዊ ሥነ-ምግባር ያለው፣ ግዳጅ የመፈፀም አቅምና ሀገራዊ ፍቅር ያለው ሰራዊት መገንባት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የመጨረሻ የኢትዮጵያ ምሽግ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረው ጀግናው ሰራዊታችን ጠላቶች የሚጮሁበት ጥንካሬውን ስለሚያውቁ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በውድ መስዋዕትነት የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ፣ ህዝብና መንግስት የሰጡትን አደራ በታላቅ ኃላፊነት የመወጣት ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡

ተመራቂ የበታች ሹም የኮማንዶ አመራሮችም በሚመዱባበቸው ክፍሎች በአርአያነትና በጀግንነት በመምራትና የሀገራችንን ሰላምና ብሄራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ለትውልዱ የማሸጋገር ኃላፊነታቸውን በታላቅ ወታደራዊ ሥነ-ምግባርና ሀገራዊ ፍቅር እንዲወጡ አሳስበዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.