Fana: At a Speed of Life!

ስለአፍሪካ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)አፍሪካ ከዓለም በስፋትና በህዝብ ብዛት ሁለተኛዋ አህጉር ስትሆን በተለይም ወጣት ሃይል የሚገኝባት ናት።

ዛሬ የአፍሪካ ቀን ነው ፤ ስለአፍሪካ የምናወራበትና የምንመክርበት ቀን ፤ቀኑ የሚከበረው የአፍሪካ ህብረት የተመሠረተበትን ቀን መነሻ በማድረግ ነው።

አፍሪካ የተፈጥሮ መትረፍረፏ የበዛላት ስትሆን መገኘት የነበረባት የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ አለመሆኗ ለብዙ ልጆቿም ይሁን ለዓለም ህብረተሰብ ውስብስብ ነው።

ለዚህም ብዙ ምክንያቶችን መደርደር የሚቻል ቢሆንም በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የትምህርት ስርዓቱና የቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ነው።

የትምህርት ስርዓት የአንድን ሀገር መፃኢ ተስፋን የሚቀርፅ አቅም አለው።

አፍሪካ የትምህርት ስርዓቷን መፈተሿ ለነገ የምተወው ሊሆን እንደማይገባ በመገንዘብ የተማረ የሰው ሃይሏን መጠቀምና ልኳን በሚያሳይ መንገድ መጓዝ ያስፈልጋታል።

ከዚህ በተጨማሪ በአፅንኦት መመልከት የሚያስፈልገው የቅኝ ግዛትን ነው። ቅኝ ግዛት የአፍሪካ የሰቆቃ ታሪኳ ሲሆን ፥ ዳግም ላለመታሠር ራስን በኢኮኖሚ ማላቅ ይጠበቃል።

ኢኮኖሚ ነፃነትን፣ ተሰሚነትን፣ ሉአላዊነትን ያስከብራል።

እንደሚታወቀው ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ሰቆቃ ውስጥ አልፈዋል፤ በተዳፈነው ወላፈንም እየተገረፉ ያሉ አሉ።

ይህን የሚያጠናክርልን ከቀናት በፊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ፥ የአፍሪካን ተሳትፎ እና አመራር በዓለም አቀፍ የሰላም እና የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ማካተት እንደሚያሥፈለግ ቢጠቅሱም ፥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ የዓለም አቀፍ አስተዳደር ዘዴዎች የተነደፉት በወቅቱ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የቅኝ ግዛት ጋር ትግል ጋር በነበሩበት ወቅት እንደነበር አስታውሰዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዓለም ቢለወጥም ዓለም አቀፍ ተቋማት ግን ባሉበት እንደሆኑም ነው ያነሱት።

በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ዓለም አቀፋዊ የደህንነት እና የልማት ችግሮችን ለመፍታት ያላትን ሚና አስመልክቶ እንዳሉት፥ “በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ ሀገራት በዚህ ምክር ቤት ጭምር በድርድር ጠረጴዛ ላይ መቀመጫ መከልከላቸውን ቀጥለዋል” ሲሉ አፍሪካ ትኩረት እንዳጣች ገልጸዋል።

በመሆኑም አፍሪካ በዓለም ሰላም እና ደህንነት ድምጿን ማሰማት እንደሚገባት ገልጸው፥ ይህንን እውን ማድረግ የሚቻለው የአፍሪካ ሀገራት በእኩልነት በዓለም አቀፍ የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ መሳተፍ ሲችሉ እንደሆነ አስረድተዋል።

በፀጥታው ምክር ቤት አናሳ የሆነውን የአፍሪካን ቋሚ ውክልና ማስተካከል እንዲሁም የእዳ አያያዝን ማሻሻል ጨምሮ የዓለም የገንዘብ ስርዓት መስተካከል እንዳለበትም ነው የጠቆሙት።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አፍሪካ ያላትን የኢኮኖሚ ሁኔታ በመጠቀም የኢኮኖሚ የበላይነት ያላቸው ሀገራት ተፅዕኖ ማሣደርና ጣልቃ መግባት ይታያል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አፍሪካ በራሷ ልጆች ጥረት በማዕበል ውስጥም ሆና ማለፍ እንደምትችል የኢትዮጵያ አልበገር ባይነትና የእህት ሀገራቶቿን ከቅኝ ግዛት የመላቀቅ ብርቱ ትግል ያሳየ ነው።

በዚህም ከኢኮኖሚ ቀኝ ግዛት ለመላቀቅ ሀገራቱና ህዝቦቻቸው እንዲሁም መሪዎች ተቀራርበው መሥራት ይገባቸዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ፓን-አፍሪካኒዝም የሁሉም አፍሪካዊ የአህጉራዊ አንድነት ማጥበቂያ ገመድ ሊሆን ይገባል።

የራስን ችግር ከራስ በላይ የሚረዳ የለምና አፍሪካ ችግሮቿን ጓዳዋን ዘግታ መክራ መፍትሄ የምታበጅ መሆን ይገባታል።

ያኔም አፍሪካ ተደማጭና ከራሷ አልፋ ለዓለም የምታዋጣው የሰላምና ደህንነት ብቻ ሳይሆን የልማት አበርክቶ ይኖራታል።

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.