Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዘንድሮውን የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዘንድሮውን የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመራቸውን ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንዳስታወቁት÷ የዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራችንን ለአቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ሶስት ባለ 9 ወለል ህንጻዎችን ልደታ ክፍለ ከተማ ላይ ወደ ግንባታ በማስገባት ጀምረናል ብለዋል።

በክረምት የቤት ግንባታ እና እድሳት ስራ 3 ሺህ 500 ቤቶችን በመገንባት 17 ሺህ 500 አቅመ ደካሞች እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተስብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡

በባለፈው የክረምት እና የበጋ የበጎ ፈቃድ ስራችን 6 ሺህ 730 ቤቶችን በመገንባት ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ችለናል ያሉት ከንቲባዋ÷ ካላቸው በማካፈል በዚህ ስራ ላይ የተሳተፉ አካላትን አመስግነዋል፡፡

ዛሬ የተጀመሩ ሶስት ባለ 9 ወለል ህንጻዎች ከቲኤንቲ ኮንስትራክሽን፣ ኢትዮ ኮቴጅ እና ከአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር እንደሚገነቡ ጠቁመዋል።

በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር 15 ዋና ዋና ፕሮግራሞችን እና 18 መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማደረግ መታቀዱንም አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.