Fana: At a Speed of Life!

በበርበራ ኮሪደር ላይ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት የአገልግሎትና የካፒታል ዝውውር ያሳልጣሉ – አቶ ተስፋዬ በልጅጌ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበርበራ ኮሪደር ላይ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት የአፍሪካን የንግድ፣ የአገልግሎት እና የካፒታል ዝውውርን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ።

በበርበራ ኮሪደር በሚኖር የሰዎች ፍልሰት ሳቢያ የሚፈጠር የጋራ ተጠቃሚነት እና ፈተናዎች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት በጅግጅጋ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ፥ የበርበራ ኮሪደር ተገማች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊ እና የጸጥታ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በርበራ ኮሪደር ልማት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ በማረጋገጥ አንድ የኢኮኖሚ ማኀበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የበርበራ ኮሪደር የስራ ዕድል እና የሰለጠነ የሰው ሃይል እንቅስቃሴን በማሳለጥ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት መግቢያ በር በመሆን እያገለገለ ይገኛል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው ፥ በበርበራ ኮሪደር ላይ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት የአፍሪካን የንግድ፣ የአገልግሎት እና የካፒታል ዝውውርን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል፡፡

በቀጠናው የሚከናወን የንግድ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በማሳደግ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚኖረው ሚና የጎላ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.