Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄን ስለሚያስገኝ ማገዝ ያስፈልጋል – ሼኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄን የሚያስገኝ በመሆኑ ማገዝ ያስፈልጋል ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ፡፡

“አንድነታችን ለሰላማችን” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ኮንፈረንስ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሄዷል።

ሼኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በዚህ ወቅት፥ የለውጡ መንግስት የጀመረው ሁለተናዊ ዕድገት ዳር እንዲደርስ ከመንግስት ጎን በመቆም ሰላምን መጠበቅም የሁላችንም ሃላፊነት መሆን አለበት ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ከሁሉም በፊት አንድነቱን ጠብቆ ሰላምን ማጠናከር ይኖርበታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ፥ ከሌሎች እምነቶች ጋር ተከባብሮና ተቀናጅቶ ሰላምን መጠበቅና አጥፊዎችን መገሰጽ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የእምነት ተቋማትም መከፋፈልን፣ ጥላቻንና ግጭትን በማውገዝ፣ ለሰላም፣ ለአንድነትና ለልማት ምዕመናቸውን በማስተማር ሚናቸውን በተግባር እንዲወጡም ነው ያሳሰቡት።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሀገራችን ችግሮች ዘላቂ መፍትሄን የሚያስገኝ ነው ያሉ ሲሆን ፥ የእርሱን ተግባር መደገፍ፣ ግብዓት መስጠት፣ መሳተፍና በማንኛውም ጉዳይ ማገዝ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን በበኩላቸው፥የአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ ሁሉም እምነቶች አንድነታቸውን ጠብቀው ለሰላምና ለልማት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

የሁሉም እምነቶች አስተምህሮ ወንድማማችነት፣ መረዳዳት፣ መተጋገዝና ፍቅር እንዲጎለብት እንደሚያስተምር ያስታወሱት አቶ አብዱ ፥ ይህም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት አቅም እንደሚሆን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.