Fana: At a Speed of Life!

በምስራቅ ቦረና ዞን በአሸባሪው ሸኔ ቡድን መሪ ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ቦረና ዞን በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደ እርምጃ ጃል ጋሞ ቤስት ወይም ዳዳቻ ሻሬ የሚባል የቡድኑ መሪ ላይ እርምጃ ሲወሰድ ሌሎች የቡድኑ ታጣቂዎች እጅ እየሰጡ መሆናቸው ተገለጸ።

በደቡብ ዕዝ የአንድ ኮር ሠራዊት እና በምስራቅ ቦረና ዞን የሊበን ወረዳ ፀጥታ ሃይሎች ልዩ ስሙ ሃርዶት ቀበሌ አካባቢ ሲንቀሳቀስ በነበረው አሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል፡፡

በዚህም የቡድኑ ሚዲያ ሃላፊና አዛዥ የነበረ ጃል ጋሞ ቤስት ወይም ዳዳቻ ሻሬ ላይ እርምጃ ተወስዶበታል ነው የተባለው።

በተጨማሪም አመራሩ ሊጠቀምበት የነበረው 02 F1 የእጅ ቦምብ፣ ከ100 በላይ የክላሽ ጥይትና የጦር መሳሪያም በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።

እርምጃ የተወሰደበት የቡድኑ መሪ ሲጠቀምባቸው በነበሩ በርካታ የማህበራዊ ትስስር ገፆች የቡድኑ የጥፋት ተልዕኮዎች የሚያራግቡና ህዝብን የሚያደናግሩ የሀሰት ትርክቶችን ሲነዛ እንደነበር መረጋገጡም ተጠቁሟል።

ይህንኑ ተከትሎ የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች ለሠራዊቱ እጃቸውን እየሰጡ ሲሆን ፥ በራስ ህዝብ ላይ የሚያደርሱትን በደል እንዲቆምና ቡድኑ ላይ እየደረሰ ባለው ከፍተኛ ኪሳራ ምክንያት እጅ እንደሰጡ ተናግረዋል።

አሸባሪው ሸኔ እየፈረሰ ይገኛል ያሉት ታጣቂዎቹ፥ ቀሪ የሽብር ቡድኑ አባላት በሰላማዊ መንገድ እጅ ከመስጠት ውጪ አማራጭ ስለሌላቸው ያላቸውን የሰላም እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ቀሪ የቡድኑ ታጣቂዎች ላይ የሚደረገው ወታደራዊ ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.