Fana: At a Speed of Life!

ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ የስለላ ሳተላይት ለማምጠቅ ማቀዷን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢሲ) ሰሜን ኮሪያ ከፈረንጆቹ ግንቦት 27 እስከ ሰኔ 4 ባለው ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ የስለላ ሳተላይት ለማምጠቅ ማቀዷን ለጃፓን አሳውቃለች።
 
ባለፈው ህዳር ወር ውስጥ የመጀመሪያውን የስለላ ሳተላይት ማምጠቋ እና ሰፊ ውግዘት ማስተናገዷም ይታወሳል፡፡
 
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ፒዮንግያንግ በዚህ ዓመት ተጨማሪ ሦስት የስለላ ሳተላይቶችን እንደምታመጥቅ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
 
ሀገሪቱ ጦሯን ለማዘመን የያዘችውን መርሐ ግብር በማስቀጠል ካለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የላቀ የጦር መሳሪያ ሙከራዎችን አድርጋለች።
 
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ የስለላ ሳተላይቶቹ ለሀገሪቱ ይጠቅማሉ የተባሉ መረጃዎችን የሚሰበስቡ ሲሆን በተለይም በደቡብ ኮሪያ ላይ እና በማንኛውም ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ወሳኝ መረጃዎችን ይሰጣሉ።
 
የጃፓን የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ሳተላይቱን ለማምጠቅ የሚያስችሉ ምህዳሮች ከትናንት እኩለ ሌሊት ጀምሮ እስካሁን ዝግጁ ሆነው መቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡
 
ሰሜን ኮሪያ የስለላ ሳተላይት ለማምጠቅ መዘጋጀቷን ያስታወቀችው በጃፓን፣ በደቡብ ኮሪያ እና በቻይና መካከል ከአምስት ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያውን የሦስትዮሽ ጉባኤ ለማካሄድ በተዘጋጁበት ወቅት ነው፡፡
 
ሰሜን ኮሪያ ዕቅዷን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ የአሜሪካ፣ የጃፓን እና የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመላክቷል፡፡
 
በዚህም ፒዮንግያንግ የባለስቲክ ሚሳኤል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሳተላይት ማስወንጨፍ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔዎችን የሚጥስ በመሆኑ እቅዱን እንድትሰርዝ ማሳሰባቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.