Fana: At a Speed of Life!

ከአፍሪካ ህብረት ሂሳብ ከ6 ሚሊየን ዶላር በላይ የምዝበራ ሙከራ የተከሰሱት እነ ቀሲስ በላይ የጠየቁት ዋስትና ውድቅ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢሲ) ከአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ክፍያ እንዲፈጸም ሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል የተከሰሱት እነ ቀሲስ በላይ መኮንን ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ቀሲስ በላይ መኮንን ጨምሮ በ5 ግለሰቦች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ እና የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከአፍሪካ ህብረት ሂሳብ 6 ሚሊዮን 50 ሺህ ዶላር ክፍያ እንዲፈጸም ሀሰተኛ የክፍያ ሰነድ በማቅረብ ከባድ ማታለል ሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ተከሳሾቹ 1ኛ ቀሲስ በላይ መኮንን፣ 2ኛ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው እያሱ እንዳለ ወ/መስቀል፣ 3ኛ በኮሚሽን ስራ ላይ የተሰማራው በረከት ሙላቱ ጃፋር፣ 4ኛ አለምገና ሳሙኤል ዲንሳ እና 5ኛ የኒሞና ንግድ ስራ ኃላ/የተ/የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አበራ መርጋ ተስፋዬ ናቸው።

ከተከሳሾቹ መካከል ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ከጠበቆቻቸው ጋር ችሎት የቀረቡ ሲሆን ሌሎቹ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በዛሬው ቀጠሮ ችሎት አልቀረቡም።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የዋስትና ክርክር ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ተሰይሟል።

ችሎቱ ስራውን እንደጀመረ በተራ ቁጥር 3 ላይ የተሰየሙት አንድ ዳኛ ከተከሳሽ ቀሲስ በላይ ጋር በሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት በግል የሚተዋወቁ መሆናቸውን ጠቅሰው ከመዝገቡ እራሳቸውን በማንሳታቸው፤ በተነሱት ዳኛ ምትክ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ ዳኛ እስኪሾም ድረስ የዛሬው ቀጠሮ በሁለት ዳኞች መዝገቡ ታይቷል።

ፍርድ ቤቱ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ባለፈው ቀጠሮ ክሱ ከደረሳቸው በኋላ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ባቀረቡት ጥያቄ መነሻ መሰረት እና በዐቃቤ ሕግ በኩል የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግ የተነሳውን የመከራከሪያ ነጥብ መርምሮ ብይን ሰጥቷል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ በወንጀል ድርጊቱ የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ክርክርን በሚመለከት በቀጣይ በፍሬ ነገር ክርክር የሚታይ መሆኑን በመጥቀስ ከድንጋጌ አንጻር ግን ተከሳሾቹ የተከሰሱበት ድንጋጌ ዋስትና የሚያስከለክል ድንጋጌ መሆኑን ተከትሎ የዋስትና ጥያቄያቸውን አለመቀበሉን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።

ከዚህም በኋላ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በባለፈው ቀጠሮ የክሱ ዝርዝር እንዲሻሻልላቸው በጽሁፍ ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ላይ ዐቃቤ ሕግ መልሱን በጽሁፍ ለችሎቱ አቅርቧል።

3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ጠበቆቻቸው ክሱን ተመልክተው የክስ መቃወሚያና የዋስትና ጥያቄ ለማቅረብ እንዲችሉ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሰረት ዛሬ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ በጽሁፍና በሶፍት ኮፒ ለችሎቱ አቅርበዋል።

ዋስትና እንዲፈቀድላቸው የመከራከሪያ ነጥቦችንም አጣቅሰው ተከራክረዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ በ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በኩል ከዚህ በፊት የተነሳው የዋስትና ጥያቄና የሰጠው መከራከሪያ መልስ ተመሳሳይ መሆኑን በመግለጽ 3ኛ ተከሳሽ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር ዋስትና በሚያስከለክል ተመሳሳይ ድንጋጌ የተከሰሰ መሆኑን ጠቅሶ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ በ3ኛ ተከሳሽ ዋስትና ጥያቄ እና ሁሉም ተከሳሾች ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያና የዐቃቤ ሕግ መልስን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የቆይታ ሁኔታቸውን በተመለከት ችሎቱ ለ3ኛ ተከሳሽ በዋስትና ጥያቄያቸው ላይ ብይን እስኪሰጥ ድረስ በማረሚያ ቤት መቆየት እንደሚፈልጉና እንደማይፈልጉ የማረጋገጫ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ ቀሲስ በላይ የጤና እክል እንዳለባቸው ጠቅሰው ባሉበት የፌደራል ፖሊስ ጊዜያዊ ማቆያ ለመቆየት እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

ከፌደራል ፖሊስ በተወከለ መርማሪ በኩል አስተያየት እንዲሰጥ ከፍርድ ቤቱ በቀረበ ጥያቄ መነሻ የጊዜያዊ ማቆያው ቦታ ጥበት መኖሩን ጠቅሶ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ እንዲደረግ ፖሊስ አስተያየት ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም እስከ ቀጣይ ቀጠሮ ግንቦት 29 ቀን ድረስ ባሉበት የፖሊስ ማረፊያ እንዲቆዩ ፈቅዷል።

4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ፌደራል ፖሊስ ተገቢ ጥረት አድርጎ አፈላልጎ እንዲያቀርባቸው ታዟል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.