Fana: At a Speed of Life!

የገበሬ ህብረት ሥራ ማህበር ከ31 ሚሊየን ብር በላይ እንዲመዘበር ያደረጉ ተከሳሾች በጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢሲ) በሰንዳፋ ከተማ ባረክ አሌልቱ የተሰኘ የገበሬ ህብረት ሥራ ማህበር ከ31 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ እንዲመዘበር አድርገዋል የተባሉ ተከሳሾች እስከ 14 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ።

ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ የግራ ቀኝ ማስረጃዎችን መርምሮ የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ነው።

የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የባረክ አሌልቱ የገበሬ ህብረት ስራ ማህበር የቦርድ ሊቀ-መንበር ተረፈ  ለማ፣  የማህበሩ ገንዘብ ያዢ  መኮንን ረጋሳ እና የማህበሩ የሂሳብ ባለሙያ አንተነህ ወጋየሁን ጨምሮ በ10 ተከሳሾች ላይ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 2 እና በዚሁ አዋጅ ስር በአንቀጽ 13 ንዑስ ቁጥር 2 እና ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

ተከሳሾቹ  በአሌልቱ የገበሬ ህብረት ስራ ማህበር ውስጥ ከጥር 23 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ ሰኔ 23 ቀን 2010 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ የሥራ ድርሻዎች ሲሰሩ ለገበሬው  የተለያዩ  ስራ ማከናወኛ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚል ምንም አይነት አገልግሎት ሳይሰጥ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ለ2 የግል ድርጅቶች ክፍያ እንዲከፈል በማድረግ በማህበሩ ላይ ጉዳት ማድረሳቸው በክሱ ተጠቅሷል፡፡

በሌላኛው ክስ ደግሞ ምንም አይነት የባንክ ደረሰኝ ባልቀረበበት ሁኔታ ላይ የገቢ መመዝገቢያ ላይ በመመዝገብ ብቻ የገቢ ደረሰኝ በመቁረጥ 10 ሚሊየን ብር ለማህበሩ ገቢ ሳይሆን እንዲመዘበር ተደርጓል  በማለት የጠቀሰው ዐቃቤ ሕግ በአጠቃላይ ከ31 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ተመዝብሯል በማለት  በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸው ነበር።

በዚህ መልኩ ክስ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል 8ኛ እና 9ኛ ተከሳሾች በቁጥጥር ስር እስኪውሉ ድረስ ለጊዜው ክሳቸው የተቋረጠ ሲሆን÷4ኛ ተከሳሽ ግን ዘግይቶ በመያዙ ተነጥሎ ጉዳዩ እየታየ ይገኛል።

ቀሪ ተከሳሾችም ችሎት ቀርበው ክሱ ከደረሳቸው በኋላ በክሱ ዝርዝር ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው÷ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የሰነድና  የሰው ማስረጃ አቅርቦ አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግን ማስረጃ መርምሮ  ተከሳሾች በተከሰሱባቸው  ድንጋጌዎች መሰረት እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ  ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ በማስረጃ አለመረጋገጡን ጠቅሶ በወ/መ/ስ /ህግ ቁጥር 141 መሰረት ነጻ ብሏቸዋል።

ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከላከሉ የተባሉ ተከሳሾች ያቀረቡትን የመከላከያ ማስረጃ ከዐቃቤ ህግ ማስረጃ ጋር በማመዛዘንና በመመርመር ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾችን በቀረቡባቸው ተደራራቢ ክሶች የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል፡፡

7ኛ እና 10ኛ ተከሳሾችም ከተሰማው ማስረጃ አንጻር ድንጋጌው ተቀይሮ ማለትም በወንጀል ህግ አንቀጽ 420 ንዑስ ቁጥር 1 እና ንዑስ ቁጥር 2 መሰረት ጥፋተኛ ተብለዋል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች  የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ጨምሮ በየደረጃው ያቀረቡትን 3 እና 4  የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ 1ኛ ተከሳሽ  ተረፈ ለማ በዕርከን 34 መሰረት በ11 ዓመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ መኮንን ረጋሳ በዕርከን 33 መሰረት በ14 ዓመት ጽኑ እስራትና በ30 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

3ኛተከሳሽ አንተነህ ወጋየሁ ፍርድ ቤቱ ያቀረበውን 3 የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በ12 ዓመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ የተወሰነ ሲሆን ÷ 7ኛ እና 10 ኛ ተከሳሽ ድንጋጌው ተቀይሮ ጥፋተኛ በተባሉበት በወንጀል ህግ አንቀጽ 420 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 መሰረት 7ኛ ተከሳሽን በ3 ወር ቀላል እስራት እንዲሁም 10ኛ ተከሳሽ  በ1 ዓመት እስራት እንዲቀጡ  ተወስኗል።

 

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.