Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የከተማ አስተዳደርና ክልላዊ የምክክር ምዕራፉን ነገ በመዲናዋ ይጀምራል

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የከተማ አስተዳደርና ክልላዊ የምክክር ምዕራፉን ነገ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚጀምር ተገለፀ፡፡

ለሠባት ቀናት በሚቆየው በዚህ የምክክር ምዕራፍ ላይ በቀዳሚነት ለምክክሩ የሚቀርቡ ተሳታፊዎች በምክክርና በውይይት የአጀንዳ ሀሳቦችን እንደሚያመጡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ(ዶ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ የሚነሱ ማንኛውንም አጀንዳዎች ለማስተናገድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ነው ኮሚሽነሩ የጠቀሱት።

በምክክሩ ላይ የሚገኙት ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግ አሰባስበውና አደራጅተው የመፍትሔ ሀሳቦችንም በዚሁ ምዕራፍ ያቀርባሉ ነው የተባለው።

በተጨማሪም የሂደቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር አጠቃላይ ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ አጀንዳዎችንና ተወካዮቻቸውን እንደሚመርጡ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

በአሸናፊ ሽብሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.