Fana: At a Speed of Life!

የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ-ጉባዔ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ-ጉባዔ መካሄድ ጀመረ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ጉባዔ ያደርጋል።

የመጀመሪያው ጉባዔ በጥቅምት ወር የሚደረግ ሲሆን÷ ሁለተኛው ርክበ ካህናት ጉባዔ በዓለ ትንሣኤ በዋለ በበዓለ ሃምሳ እኩሌታ በዕለተ ረቡዕ የሚካሄደው ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በጉባዔው መክፈቻ ባስተላለፋት መልዕክት÷ከኦርቶዶክሳዊ ቀኖናና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች በቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ላይ አደጋ ደቅነዋል ብለዋል።

ችግሮችን በውይይትና በጥበብ እንዲሁም በሕግ ማረም ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል።

ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለመስጠት አንድነትንና ሰላምን ግብ በማድረግ ሕግና ሥርዓትን የተከተለ ውይይትና ምክክር ማድረግ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ያስችላል ብለዋል።

በቤተክርስቲያንና በሀገር ላይ በየጊዜው የተለያዩ ችግሮች እያጋጠሙ መሆኑንም ገልፀዋል።

በደልን በካሳና በእርቅ፣ በይቅርታና በምህረት በመዝጋት ተመሳሳይ በደል እንዳይፈፀም አስተማማኝ ተቋማዊ ሥርዓት ማበጀት ይገባልም ነው ያሉት።

ጉባዔው በዚህ ጉዳይ በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ ሁሉንም ሊያስማማ የሚችልና ወደ ሰላምና ዕርቅ ሊያደርስ የሚችል ሥራ መሥራት ይኖርበታል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንዲችሉና ለሀገር ህልውናና ደኅንነት ቤተክርስቲያን የበኩሏን ኃላፊነት ለመወጣት ጠንክራ መሥራት ይኖርባታል ሲሉም ተናግረዋል።

ምልዓተ-ጉባዔው ወቅታዊና ወሳኝ ሐዋርያዊና ቀኖናዊ በሆኑ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለቤተክርስቲያንና ለሀገር ጠቃሚ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.