Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በታዳጊ ሀገራት ፍትሃዊና ጥራት ያለዉ የጤና አገልግሎት ለማቅረብ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቀረበች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በታዳጊ ሀገራት ፍትሃዊና ጥራት ያለዉ የጤና አገልግሎት በተሟላ መልኩ ለማቅረብ የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ የሚመለከታቸዉ አጋሮችና ባለድርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርባለች።

በስዊዘርላንድ ጀኔቫ እየተካሄደ ባለዉ 77ኛዉ የዓለም ጤና ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በተለያዩ የጤና ጉዳዮች ላይ መግለጫ አቅርባለች፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ለጉባኤው ባደረጉት ንግግር፥ የጤና አገልግሎት የዜጎች ሰብዓዊ መብት መሆኑን ኢትዮጵያ በጽኑ ታምናለች ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ማንንም መተዉ የለበትም በማለት ገልጸው፤ ምንም ዓይነት ልዩነትና ድንበር ሳይኖር ጥራት ያለዉ የጤና አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ቤተሰብን ማዕከል በማድረግ በተሰሩ የጤና ስራዎች በተለይም በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በገጠርና ራቅ ባሉ አካባቢዎች ላሉ ዜጎች ጭምር ግንዘቤ በመፍጠርና መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በማቅረብ አመርቂ ዉጤቶች መገኘቱን ገልጸዋል።

በተለይም የእናቶችና የህጻናት ጤናን በማሻሻል ሞትን መቀነስ፣ ኮቪድ- 19ን ጨምሮ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ከመከላከልና መቆጣጠር አንጻር በተሰሩ ስራዎች ቀላል የማይባል ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ግን የጤና አደጋዎችን የሚቋቋምና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ የጤና ስርዓት እንዲገነባ አሁንም ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የጤና አገልግሎት የዜጎች ሰብዓዊ መብት ሆኖ እያለ በቂ ሃብት ባለመኖሩና በሌሎች ምክንያቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ ሀገራት ለዜጎች ፍትሃዊና ጥራት ያለዉ የጤና አገልግሎት በተሟላ መልኩ ለማቅረብ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ አጋር ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ በዓለም አቀፍ የጤና ሽፋን ተደራሽነትና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ ቀጣይነት ያለዉ የጤና ፋይናንሲንግ እና የአባል ሀገራት አስተዋጽኦ እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት ድንገተኛ የጤና አደጋ፣ ዓለም አቀፍ ጤናና ሰላም ኢኒሼቲቭና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ የተዘጋጁ መግለጫዎች በኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ተወካዮች ቀርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.