Fana: At a Speed of Life!

የህብረተሰብ ተወካዮች በአጀንዳ ሃሳቦች ላይ እያደረጉት ያለው ውይይት እንደቀጠለ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛ ቀኑን ያስቆጠረውና የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ እያስተባበረ የሚኘው የምክክር ምዕራፍ ዛሬም ቀጥሏል፡፡

ከትናንት ግንቦት 21 ቀን 2016 ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በነበረው መርሃ-ግብር ተሳታፊዎች በየህብረተሰብ ክፍላቸው በቡድን በመሆን ከወከሉት ማህበረሰብ በአደራ ያመጧቸው የአጀንዳ ሀሳቦች ላይ ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

በሂደቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የኛ የሚሉትን እና የተስማሙባቸውን የአጀንዳ ሀሳቦች በማጠናቀር ለኮሚሽኑ በቃለ-ጉባኤ ተፈራርመው ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እነዚህ የአጀንዳ ሀሳቦችም በቀጣዮቹ ቀናት በሚኖሩ መድረኮች በተወካዮቻቸው አማካኝነት የሚንፀባረቁ ይሆናል፡፡

ዛሬ ከሰዓት በሚኖረው መርሃ-ግብርም ተሳታፊዎች በቀጣዮቹ የምክክር ምዕራፎች ላይ የሚወክሏቸውን 121 ተወካዮች በመምረጥ ለሚቀጥሉት የምክክር ምዕራፎች ይዘጋጃሉ፡፡

ኮሚሽኑ እያስተባበረ የሚቆየው ይህ የምክክር ምዕራፍ በቀጣዮቹ ቀናት ተጨማሪ የአራት ባለድርሻ አካላት ተወካዮችን በማሳተፍ እየተከናወነ  እንደሚቀጥል የኮሚሽኑ መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.