Fana: At a Speed of Life!

በቴል አቪቭ በኤርትራውያን ስደተኞች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በእስራኤል ቴል አቪቭ በኤርትራውያን ስደተኞች መካከል በተፈጠረ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉ ተገለፀ፡፡

ግጭቱ በኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ እና ደጋፊ በሚል በሁለት ጎራ በተከፈሉ ኤርትራውያን ስደተኞች መካከል የተፈጠረ ሲሆን አንድ ሰው በስለት ተወግቶ ህይወቱ ማለፉን ፖሊስ እና የህክምና ባለሙያዎች አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም በግጭቱ አምስት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የተገለፀ ሲሆን፤ ከአምስቱ ውስጥ ሶስቱ ለሞት የሚያደርስ ከባድ የአካል ጉዳት አስተናግደዋል ነው የተባለው፡፡

ግጭቱን ተከትሎ የእስራኤል ፖሊስ 20 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና ህይወቱ ያለፈውን ሰው በተመለከተ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የእስራኤል ፖሊሶች ግጭቱን በማርገብ ሰላም ለማስከበር በቴል አቪቭ አካባቢ ተሰማርተው በግጭቱ ተሳትፎ እንዳላቸው የተጠረጠሩ ሌሎች ሰዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ባለፈው ዓመት መስከረም ወር በተመሳሳይ ጎራ በለዩ የኤርትራ ስደተኞች መካከል በተፈጠረ ግጭት የፖሊስ ኦፊሰርን ጨምሮ 70 ሰዎች መጎዳታቸውን ያስታወሰው የዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘገባ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.