Fana: At a Speed of Life!

ህብረተሰቡ ከመጭበርበር የወንጀል ድርጊት እንዲጠነቀቅ አገልግሎቱ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ህብረተሰቡ ከመጭበርበር የወንጀል ድርጊት እንዲጠነቀቅ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አሳሰበ፡፡

አገልግሎቱ አንዳንድ ግለሰቦች እና የወንጀል ድርጊት ፈፃሚዎች የተለያየ ገጽታ ያላቸው ወንጀሎች በመፈጸም በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ለማግኘት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን  መረጃ  ደርሶኛል ብሏል፡፡

ቀደም  ሲል የኦንላይን እና ልዩ ልዩ ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም የትርፍ ጊዜ ሥራ፣ አማራጭና አዋጭ ስራ እንዲሁም ኢንቨስትመንት የሚል ማደናገሪያ ስልቶችን  በመጠቀም ግለሰቦችን በኦንላይን በመቅረብና ግንኙነት በመፍጠር ወደ ማጭበርበሪያ ሰንሰለት ውስጥ በማስገባት ገንዘብ ወስደው ሲሰወሩ መቆታቸውን  አስታውሷል።

በኦንላይንና ማህበራዊ ሚዲያ የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ሀሰተኛ ስም እና አድራሻ በመጠቀም እንዲሁም መቀመጫውን በውጭ አገራት አድርገው በአንዳንድ መሰል ድርጊት ላይ ከተሰማሩ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር  የወንጀል ድርጊቱን ሲፈጽሙ የነበሩ ናቸው ብሏል።

እነዚህ አካላት በውጭ አገራት ያሰባሰቡትን ገንዘብ በአገር ውስጥ የወንጀል ድርጊቱ ተባባሪ በሆኑ ግለሰቦች አማካኝነት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በኢትዮጵያ ብር ለተለያዩ ግለሰቦች እንዲከፈል እና ተመጣጣኝ መጠን ያለው ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ እንደሚከፍሉ በማግባባት የውጭ አገራት ምንዛሪን ይዘው የመሰወር የወንጀል ድርጊት እንደመፈፅሙም ገልጿል፡፡

እነዚህ አካላት በህገ-ወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ምንዛሪ ላይ በመሰማራት የወንጀል ድርጊት ከመፈጸም ባሻገር የውጭ አገር ምንዛሪውን ይዘው በመሰወር በአንድ በኩል በግለሰቦች ላይ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በህጋዊ መንገድ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛሉ ብሏል።

ስለሆነም ህብረተሰቡ የማጭበርበር እና መሰል የወንጀል ድርጊት ሰለባ እንዳይሆን እንዲጠነቀቅ አገልግሎቱ አሳስቦ  መሰል የወንጀል ድርጊቶች ጋር ግንኙነት ያለው አጠራጣሪ ጉዳይ ሲመለከት በስልክ ቁጥር +251-11-812-8261 ወይም በአካል በመገኘት ጥቆማ እንዲሰጥ መልዕክቱን  አስተላልፏል፡፡

ስለሆነም እነዚህን አካላት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚሰራው ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ ህብረተሰቡ የማጭበርበር እና መሰል የወንጀል ድርጊት ሰለባ እንዳይሆን ራሱን እንዲጠብቅና እንዲጠነቀቅ አገልግሎቱ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም መሰል የወንጀል ድርጊቶች ጋር ግንኙነት ያለው አጠራጣሪ ጉዳይ ሲመለከት በስልክ ቁጥር +251-11-812-8261 ወይም በአካል በመገኘት ጥቆማ እንዲሰጥና የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አገልግሎቱ  ጥሪ አስተላልፏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.