ሀሰተኛ ሰነድ የሚያዘጋጅን ግለሰብ ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ሀሰተኛ ሰነድ የሚያዘጋጅን ግለሰብ ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 በሚገኘው የግለሰቡ መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ የ29 የመንግስትና የግል ተቋማት ክብ ማህተሞች፣ ብዛታቸው 26 የልዩ ልዩ የስራ ኃላፊ ቲተሮች በኤግዚቢትነት መያዙ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም በግለሰቡ አማካኝነት የተዘጋጁ የወሳኝ ኩነት ሰነዶች ፣ የተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ፣ የሰራ ልምድ ፣ የነዋሪነት መታወቂያ ፣ ልዩ ልዩ ደብዳቤዎችና ሰነዶችን በኤግዚቢትነት ይዞ ምርመራው መቀጠሉን አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ህገወጥ ተግባሩን ሲፈፅም እንደነበር በማስረጃ ተረጋግጧል ነው ያለው ፖሊስ፡፡
መንግስታዊ ፣ የግልና ሌሎች ተቋማትም ለልዩ ልዩ ጉዳዮች የሚቀርቡላቸውን ሰነዶችና መታወቂያዎች ትክክለኛነት የማረጋገጥ ተግባር ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባና ህብረተሰቡም መሰል ወንጀሎች ሲያጋጥመው ለፖሊስ ጥቆማ መስጠቱን ሊቀጥል እንደሚገባ አዲስ አበባ ፖሊስ መልእክቱን በገጹ አስተላልፏል።