Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ሰላምን መርጠው ለሚመጡ እጁን ዘርግቶ ይቀበላል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ሰላምን መርጠው ለሚመጡ እጁን ዘርግቶ ይቀበላል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ፥ ገዳን የመሰለ ባህል እንዳለው ማህበረሰብ ስለሰላም እንሰብካለን ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ነገውን የሚያቀናው በጠመንጃና ጫካ በመግባት ሣይሆን ህገ መንግስታዊ መብቱን በመጠቀም መሪዎቹን በመምረጥ ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም ግን አሁንም ታጣቂ ቡድኖች ጫካ ሆነው በህዝቡ ላይ የሚያደርሱት ግድያ እና ስቃይ የሚወገዝና አሳፋሪ ተግባር ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በዚህም የተባበረና ኃላፊነት የሚሰማው ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን “ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት፣ ሰላምና መረጋጋት ይስፈን” ሲሉም ገልጸዋል አቶ ሽመልስ።

ምክንያቱን ሲያስረዱም ፥ በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እንዲያበቃ እና በሰላም የመኖር፣ የመስራት እና የመልማት እድልን እንፈልጋለን ብለዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ከዚህ ቀደም የከፈለው መስዋዕትነት ለዛሬው ለዘመናዊ የፖለቲካ ምርጫ መንገድ የጠረገ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ የፖለቲካው መድረክ በተከፈተበት ወቅት በተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች የተነሳ ሃሳብን ማፈን፣ መብት አለማክበር እና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ታሪክ እየሆነ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ሃሳብን በነጻ ማንሸራሸር፣ የፖለቲካ ተሳታፎ እና ውድድር፣ በኃላፊነት የመምራት እና ህዝብን የማገልገል እድል መፈጠሩን ገልጸው ፥ ተቋሞቻችንን ለማጠናከር ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ይህንን የሚደግፉ ህጎችና ሥርዓቶች እየተዘጋጁ ነው ብለዋል።

አሁንም የኦሮሚያ ክልል መንግስት የሰላም ጥሪውን ያቀርባል ያሉት አቶ ሽመልስ ፥ በአሁኑ ወቅት የሸኔ ቡድን አባላት እጃቸውን ለመንግስት በመስጠት በተሃድሶ ፕሮግራም እያለፉ እንደሆነም ጠቁመዋል፤አሁንም በዚህ ሂደት ላይ ያሉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

የሀዘንና የግጭት ምዕራፍን በመዝጋት የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር መድረክ መቅረቡን ገልጸው ፥ መንግሥትና ሕዝብ ወደ ግጭት አፈታት በመሸጋገር ለውይይትና ድርድር በራቸውን መክፈታቸውን ገልፀዋል፡፡

በዚህም ” በታጣቂ ሃይሎች የሚደርሰው ስቃይ፣ ግድያ እና ዘረፋ እንዲቆም እያሳሰብኩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪዬን አቀርባለሁ “ብለዋል።

የኦሮሚያ አካባቢዎችን ወደቀድሞ ሰላሙ እንመልስ ፤ ሰላምን ለመረጡ እና ወደ ቤተሰባቸው ለመመለስ ለሚፈልጉ፣ ያለምንም ማመንታት ተመለሱ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ለሰው ልጆች እና ባህላችንን በሚመጥን ክብር ልንቀበላችሁ ዝግጁ ነን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ መንግስት ለሰላም እጁን ዘርግቶ እንደሚቀበልም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.