Fana: At a Speed of Life!

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በመሆን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በመሆን በዛሬው እለት ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር አካሂደዋል።

የብልጽግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ (ኢሶዴፓ)፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት በየካ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የሚሌኒየም ፓርክ ችግኝ ተክለዋል።

የዛሬው የችግኝ ተከላ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ለመትከል የታቀደው የ7 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ እቅድ አካል ነው።

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መግባባት በሚያስፈልጋቸው አጀንዳዎች ላይ በትብብር አለመስራታቸው የኢትዮጵያን እድገት ወደ ኋላ መጎተቱን ገልጸዋል።

ይሁንና በአሁኑ ሰአት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ለመስራት ያላቸው ፍላጎት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በመጠቆም፤ በትብብር ለመስራት እያሳዩት ያለው አቋምም ጅምሩ መልካም መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን የመቋቋምና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ለአንድ አካል የሚተው ባለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ላይ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው ”የተፎካካሪ ፓርቲዎች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሳትፎ ማድረግ በሌሎች ሀገራዊ አጀንዳዎች በትብብር የመስራት መንፈስን ያጠናክራል” ብለዋል።

የአዲስ አበባ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ በአረንጓዴ አሻራ ላይ የታየው ትብብር በሌሎች ሀገራዊ አጀንዳዎችም ላይ ሊደገም እንደሚገባው ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የተተከሉ ችግኞችን በዘላቂነት በመንከባከብ ለአረንጓዴ አሻራ ስራው መሳካት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አቶ ተስፋዬ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግብል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.