Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች የህዳሴ ግድብን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የክልል ርእሳነ መስተዳድሮችና ምክትል ርእሳነ መስተዳድሮች የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎበኙ።

በጉብኝቱ ላይም የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የአፋር፣ የሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እንዲሁም የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርእሰ መስተዳድሮች እና ምክትል ርእሰ መስተዳድሮች ተሳትፈዋል።

የሰባቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች በኢኖቬቭንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም በላይ እና በተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ በመመራት የግድቡን ግንባታ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም በግድቡ ላይ ስለተከናወኑት ተግባራትና በመጪው ክረምት ውሃ ለመያዝ የሚሰሩትን ስራዎች በተመለከተ ገለፃ አድርገውላቸዋል።

በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትልልቅ ስራዎች በሚሰሩበት ጊዜ ርዕሰ መስተዳድሮቹ ግድቡን መጎብኘታቸው የተለየ ትርጉም እንደሚሰጠውም ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሮቹ እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮቹ በበኩላቸው የግድቡ ወቅታዊ የግንባታ ሂደት አበረታች እንደሆነ መመልከታቸውን ገልፀዋል።

ይህም ስለግድቡ ለሚመሩት ህዝብ በተገቢው ሁኔታ ለመግለፅና በተለያዩ ወገኖች የሚሰነዘሩ አሉታዊ አስተያየቶችን ለማክሸፍ ያስችለናል ብለዋል።

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ከጉብኝቱ በኋላ ግድቡ እየተገነባ ባለበት ስፍራ ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመካከለኛው ክፍል የኮንክሪት ሙሊት ለዓመታት ከነበረበት ከባህር ጠለል በላይ ከ525 ሜትር አሁን ላይ 552 ሜትር ደርሷል።

ውሃ ለመያዝም ስምንት ሜትሮች ብቻ የቀሩት ሲሆን፥ የግድቡ ግንባታ አጠቃላይ አፈፃፀም 74 በመቶ መድረሱን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.