Fana: At a Speed of Life!

የዞረ/ቆልማማ እግር ምንነት እና መፍትሔው

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቆልማማ እግር ወይም የዞረ እግር በውጩ ቋንቋ አጠራር ደግሞ “ክለብ ፉት” ህፃናት በሚወለዱበት ጊዜ አንድ ወይም ሁለት እግራቸው ወደ ውስጥ መዞር የሚታይበት እክል ነው፡፡

በዚህም ህፃናት ሲወለዱ ችግሩ ያለባቸው ስለመሆኑ አይቶ ለመለየት የሚያስቸግር ባይሆንም የህክምና ባለሙያ አይቶ የእግር መቆልመም ነው አይደለም የሚለውን መለየት እንደሚያስፈልግ ነው የሚገለጸው፡፡

አብዛኛውን ጊዜ የዞረ እግር ይህ ነው የሚባል መንስዔ ወይም በምን እንደሚመጣ ምክንያቱ ባይታወቅም ከተጓዳኝ ችግሮች ጋር ተያይዞ ሊከሰት እንደሚችል ባለሙያዎቹ ያነሳሉ፡፡

እንዲሁም መሰል ችግር በተወሰነ መልኩ በቤተሰብ ውስጥ ካለ ሊተላለፍ እንደሚችልም ነው የሚገለፀው፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ህብረተሰቡ ስለችግሩ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳለውና ከእርግማን፣ ከቁጣ፣ ከሃጢያትና ከሀይማኖት ጋር ምንም የተያያዘ እንዳልሆነ ህብረተሰቡ መረዳት እንዳለበት የህክምና ባለሙያዎች መልዕክት ያስተላለፉት፡፡

ህክምናውን በተመለከተ ደግሞ ቀደም ሲል የዞረውን እግር ለማስተካከል ቀዶ ህክምና ይደረግ የነበረ÷ አሁን ላይ ግን ያለ ቀዶ ህክምና በቀላሉ ማከም የሚቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ነው የሚነገረው ፡፡

እሱም “Ponseti” ህክምና ሲሆን÷ በዚህም ህፃናት እስከ አምስት አመታቸው ድረስ በተለያየ የህክምና ሁኔታ ደረጃ በደረጃ ክትትሉ ቆይቶ የሚታከም መሆኑ ይገለጻል።

ይህም ሊሆን የቻለው የችግሩ ተጋላጭ ህጻናት እስከአምስት አመታቸው ድረስ የመመለስ እድል ስለሚኖረው እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡

በአጠቃላይ የዞረ/ቆልማማ እግር ችግር በጊዜ ታይቶ ህክምና ከተጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቀላሉ እንደሚስተካከል ነው የሚነገረው፡፡

በጊዜ ካልታከመ ግን ለዘላቂ የአካል ጉዳት እንደሚያዳርግ ነው የህክምና ባለሙያዎች አፅንዖት ሰጥተው የሚናገሩት፡፡

እንዲሁም ህፃናት ሲወለዱ አብሮ የሚወለድ እንጂ ከዛ በኋላ ባለው ጊዜ የሚከሰት ችግር እንዳልሆነም ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

በሀገራችንም ከዚህ ችግር ጋር በየአመቱ በርካታ ህፃናት እንደሚወለዱ ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.