Fana: At a Speed of Life!

በሀረሪ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀረሪ ክልል ኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ተናገሩ።

በሚኒስትር ዲኤታው የተመራው የልዑካን ቡድን በሀረሪ ክልል ተገኝቶ ኮቪድ-19ን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተቋቋሙ አምስት የተለያዩ የለይቶ ማቆያና ህክምና መስጫ ማዕከላት እንዲሁም ሁለት የላቦራቶሪ ምርመራ ማዕከላትን ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ላይ ዶክተር ደረጀ በክልሉ በሚገኙ ለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማዕከላት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው ህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋትና ግድ የለሽነት በፍጥነት መስተካከል አለበት ብለዋል።

በየደረጃው ያለው አመራር፣ የጤና ባለሙያና ሁሉም ባለድርሻ አካላትም በህብረተሰቡ ዘንድ የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ መስራት ይገባቸዋልም ነው ያሉት።

በተያያዘም ሚኒስትር ዲኤታው ከሐረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ጋር በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከመግታት አንጻር እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ በክልሉ የተቋቋሙ ለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማዕከለትን ርዕሰ መስተዳድሩ በቅርበት እንደሚከታተሉና አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በህብረተሰቡ ዘንድ እየታየ ያለውን መዘናጋት ለማስተካከል በትጋት መሰራት እንዳለበትም መክረዋል።

በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝም የፌደራሉ መንግስት ለክልሉ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው የፌደራል መንግስት አቅም በፈቀደ ሁሉ ለክልሎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.