Fana: At a Speed of Life!

የምድር ድንቅ ስጦታን ከስጋት ለመታደግ …

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምድር ለሰው ልጆች ያበረከተችውን ድንቅ ስጦታ በአግባቡ ጠብቆ ባለማቆየትና ባለመጠበቅ መልሰን እያጣነው ይመስላል፡፡

አካባቢ ማለት በዙሪያችን ያሉት ህይወት ያላቸውና የሌላቸው ነገሮች ድምር ውጤት ሲሆን በከባቢው ውስጥ የሚኖረው ሥነ-ፍጥረት መስተጋብሩን ጠብቆ መሄድ ካልቻለ ለኑሮ ዋስትና ስጋት መጋረጡ አይቀሬ ይሆናል።

የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ50ኛ እንዲሁም በሀገር ደረጃ ደግሞ ለ31ኛ ጊዜ ‘የተጎዳ መሬት እንዲያገግም የእንክብካቤ ሥራ እንስራ፤ በረሃማነትና ድርቅን ለመቋቋም የመሬት ማገገምን ማረጋገጥ’ በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ይገኛል፡፡

በዚህም ዕለት ስለአሁናዊ ከባቢ ሁኔታ፣ ስለአሳሳቢው የዓየር ንብረት ለውጥና መፍትሄዎቹ፣ ስለምድር መጻዒ እጣ ፈንታና የሰው ልጆች ተጽእኖ እንዲሁም መሰል ጉዳዮች ላይ ዓለም በጥብቅ መወያየት ያስፈልጋታል፡፡

እርግጥ ነው ቀኑ ምክንያት ቢሆን እንጂ በዚህ ጉዳይ ዓለም በቀጠሮ መክሯል፤ ሀገራት ይሆናል ያሉትን ሃሳብና ገንዘብ አዋጥተውበታል፡፡

ሆኖም አሁን ካለው የዓለም የአካባቢ ሁኔታ ጋር ሲታይ የተደረገው ጥረት በቂ እንዳልሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡

በተለይም ያደጉ ሀገራት በግዙፍ ኢንዱስትሪዎቻቸውና ለአካባቢ ዓየር ብክለት የሚያጋልጡ ተግባሮቻቸውን እንዲገድቡና በአንጻሩ ለችግሩ መፍትሄዎችን እንዲጠቁሙ ግፊት ቢደረግባቸውም የዓለም ከባቢ ንብረት ወደ ስጋት መክተታቸውም ገፍተውበታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት የጎላ ድርሻ ሳይኖራቸው የዓየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል።

በዚህም ለጎርፍ፣ ለመሬት መንሸራተት፣ ከፍተኛ ሙቀትና ድርቅ እንዲሁም ሌሎች አደጋዎች ተጋላጭ ሆነዋል።

አደጋዎቹ ማንቂያ ደወል ተደርገው ሊወሰዱና ለመፍትሄ መንቃት ያስፈልጋል። በዚህም ወደ ስራ ከተገባ የደረቁ ምንጮች ይፈልቃሉ፤ ጥም ያዛላቸው ዕጽዋት ለመስካቸው ውበት ለእንስሳት መኖ ይሆናሉ፤ ዓለም ሚዛኗን ትጠብቃለች፡፡

ሁሉም ሀገር ለዓየር ንብረት ለውጥ የራሱን ጠጠር ሲጥል ዓለም እየደረሰባት ካለና ከሚመጣባት ቅስፈት በትንሹም ቢሆን ታገግማለች፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያ ለዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ያጣቻቸውን እስትንፋሶቿን በተለያዩ የንቅናቄ ስራዎች ለመመለስ እየተጋች ሲሆን፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን ተክላለች፤ አሁንም አጠናክራ እየሰራችበት ነው።
በሰጧት ልክ መልሳ የምትሰጠው ተፈጥሮ በሚደረግላት እንክብካነቤና ጥበቃ የተጋረጠውን የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም ያስችላል።

ሆኖም መሰል እንቅስቃሴዎች በጥቂት ሀገራት ብቻ በመደረጋቸው የዓለም የዓየር ንብረት ለውጥ ወደቀደመ ቦታው ሊመለስ እንደማይችል እሙን በመሆኑ፤ ሀገራት እየወሰዱት ያለውን እርምጃ በማጤን ዓለም ከገባቸበት ችግር እንድትወጣ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ካደጉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በዓየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርስባቸው ተጽዕኖ የከፋ በመሆኑ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በእነዚህ ሀገራት ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ የአካባቢ ተቆርቋሪ ወገኖች ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት የዓየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን አደጋ ለመቋቋም ሲጠይቁት የነበረውንና እየጠየቁት ያለው የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ነው፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት በተካሄደው የዓለም ምጣኔ ሃብት ጉባዔ ላይ በወጣው ሪፖርት ዓለም በ2050 በዓየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 12 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር ስታጣ ችግሩ የ14 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎችን ሕይወት እንደሚቀጥፍ ተመላክቷል፡፡

በሞቃታማ የዓየር ንብረት ቀጣና ባሉ ሀገራት የሚኖሩ 500 ሚሊየን ያህል ሰዎችም በዚሁ በሚዛመቱ እንደ ወባ፣ ዴንግ እና ዚካ ያሉ በሽታዎች እንደሚጠቁም ነው የተጠቆመው፡፡

ሪፖርቱ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር ይመዘገባል ብሎ የተነበየው ከጎርፍ እና ከድርቅ የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተያይዞ መሆኑም ተነግሯል፡፡

ዓለም 12 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላሩን የምታጣው ከሙቀት መጨመር፣ ድርቅ እና የጎርፍ አደጋ ጋር በተገናኘ በምታስተናግደው የምጣኔ ሐብት ተፅዕኖ መሆኑንም ያሳያል የሪፖርቱ አሃዛዊ መረጃ፡፡

ተፅዕኖው በቀዳሚነት የእስያ ሀገራትን ሲጎዳ አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ በሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ገፈት ቀማሽ እንደሚሆኑም ነው ሪፖርቱ ያመላከተው፡፡

በዓየር ንብረት ለውጥ የእስያ ሀገራት 3 ነጥብ 5 ትሪሊየን፣ አውሮፓ 2 ነጥብ 6 ትሪሊየን እንዲሁም ደቡብ አሜሪካ 2 ነጥብ 2 ትሪሊየን ዶላር ተብሏል፡፡

በዚህም በቀደሙት የዓየር ንብረት ለውጥ ስብሰባዎች የተደረሱ ስምምነቶች በአስቸኳይ ከተተገበሩና የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤዎችን ለመግታት ሙከራ ከተደረገ የምድርን ደህንነት ማስጠበቅ ይቻላል። ምድርም ባደረግንላት ጥበቃና እንክብካቤ ልክ መልሳ ትሰጠናለች።

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.