Fana: At a Speed of Life!

አቶ ርስቱ ይርዳው በሶዶ ወረዳ እየተከናወኑ ያሉ የኢንቨስትመንት ስራዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በጉራጌ ዞን በሶዶ ወረዳ አስተዳደር እየተከናወኑ ያሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች ጎበኙ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ጋር በመሆን በወረዳው ቡኢ ከተማ በ240 ሚሊየን ብር በቻይና ባለሃብቶች እየተገነባ ያለውን የችፑድ ፋብሪካ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ፋብሪካው ለ300 ሰራተኞች ቋሚ እንዲሁም ለ700 ሰራተኞች ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥር የተገለጸ ሲሆን ወደ ምርት ሲገባም በዞኑ በአራት ወረዳዎች ከሚገኙ አርሶ አደሮች የነጭ ባህር ዛፍ ግብአት የሚያገኝ ሲሆን ከዘርፉ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ተብሏል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ የተገነባውን እና 132 ኪሎ ቮልት የመሸከም አቅም ያለውን የቡኢ ኤሌክትሪክ ሀይል ማከፋፈያ ጣቢያም ጎብኝተዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በደቡብ ክልል የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ስኬታማ እንዲሆኑ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በዘርፉ የሚገጥሙ ችግሮችን በመፍታት ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ጥረት ይደረጋልም ነው ያሉት።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በሶዶ ቡኢ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤት ላይ ተገኝተው ችግኝ መትከላቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.