Fana: At a Speed of Life!

በአርሲ እና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአረንጓዴ አሻራና የበጎ ፈቃድ ቀን ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአርሲ እና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአረንጓዴ አሻራና የበጎ ፈቃድ ቀን ተካሄደ ።

በመርሃ ግብሩ የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳና የማዕድ ማጋራት ተካሂዷል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት እንደሀገር የተጀመሩ ስራዎችን ለመደገፍ ታቅዶ መርሃ ግብሩ መካሄዱን አንስተዋል።

አያይዘውም ትምህርት ተቋማቱ ከሚሰሯቸው መደበኛ ስራዎች ጎን ለጎን በመሰል ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ይሳተፋሉ ነው ያሉት።

በአርሲ ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በኮሮና መከላከልና መቆጣጠር የሰራቸው ተግባራት ተጎብኝተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዱጉማ አዱኛ ኮሮናን ከመከላከል ጎን ለጎን በተያዘው ክረምት ከ60 ሺህ በላይ ሃገር በቀል ችግኞችን ተክሎ ለማፅደቅ ማቀዱን ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ጉብኝት፣ የደም ልገሳ፣ የችግኝ ተከላና የማዕድ ማጋራትም ተካሂዷል።

በተያያዘም የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ “የአረንጓዴ አሻራ ቀን” ለሁለተኛ ዙር በዩኒቨርሲቲዉ ሁሉም ግብዎች ከ35 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል አሻራውን አኑሯል።

የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ በነበረው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ከተጠበቀው በላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉን ገልፀው ችግኞች እንዲፀድቁ በተቀናጀ ሁኔታ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

በአፈወርቅ እያዩ እና አስጨናቂ ጉዱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.