Fana: At a Speed of Life!

የፒያሳና የአራት ኪሎ መስመር ስራ በተያዘው የ3 ወር መርሐ ግብር ማጠናቀቃችንን ስገልፅ ደስታ ይሰማኛል- ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፒያሳ እና የአራት ኪሎ መስመር ስራ በተያዘው የሶስት ወር መርሃግብር ማጠናቀቃችንን ስገልፅ ደስታ ይሰማኛል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የቀደሙትን የኮሪደር ልማት ስራዎች ግምገማ ስናጠናቅቅ ቀጣዩን ግምገማችንን በስራው ስፍራ ተገኝተን እንደምናካሂድ ቃል ገብተን ነበር ብለዋል።

በዚህም የፒያሳ እና የአራት ኪሎ መስመር ስራ በተያዘው የሶስት ወር መርሃግብር ማጠናቀቃችንን ስገልፅ ደስታ ይሰማኛል ሲሉ ገልጸዋል።

በቀጣይ ስራ ሀብት ቁጠባ ቀዳሚ ትኩረት ሆኖ በቀሪ ኮሪደሮች ስራዎቻችን ፈጣን እና ፈጠራ መር ልንሆን ይገባል ብለዋል።

ጥራትን ማስጠበቅ እና ለዜጎቻችን ሁሉ የተመቸ ከባቢን መፍጠር ቅድሚያ የምንሰጣቸው ተግባራት ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

ይህ ፕሮጀክት የሚራመደው በብዙሃን ትብብር መሆኑን ጠቅሰው ከጅማሮው በስራችን ባገኘነው በጎፈቃድ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።

ይህም በእቅድ እና አፈፃፀም ላይ የታየውን ጥረታችንን እና መልካም ፈቃዳችንን የመጠነ ሆኖ ታይቷል ነው ያሉት።

በዚህ ከተማችንን ለተሻለ ለውጥ ለማብቃት በተደከመበት ታላቅ ስራ ሂደት ውስጥ በዜጎቻችን ላይ ፈጥረነው ሊሆን ለሚችል አለመመቸት ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያችን እንድትለወጥ በፅናት እንደምንሰራ በዚህ የኮሪደር ልማት ስራ ሂደትም ያሉ የዲዛይን እና የጥራት ክፍተቶችም ካሉ ማስተካከል እንደምንቀጥል እንድትተማመኑ ለመግለፅ እፈልጋለሁ ብለዋል።

በግሉ ዘርፍ ያሉ አጋሮቻችንን ጨምሮ ትናንት ምሽት በጎዳናዎች ፍቅራችሁን ለገለፃችሁልን፤ በአጠቃላይም በዚህ ስራ ለተሳተፋችሁ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.