Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ሪፎርም እንዲፋጠን ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሀገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ሪፎርም እንዲፋጠን ጠይቀዋል፡፡

የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ሪፎርምን በማስመልከት የአፍሪካ ህብረት ከ10 ሀገራት የተውጣጣው የሚኒስትሮች ኮሚቴ 11ኛው ጉባኤ በአልጀርስ ተካሂዷል፡፡

በዚህም የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ፣ የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር ባንኮሌ አዲኦዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡

ይህ ለውጥ በፍጥነት እንዲተገበርም በአፍሪካ ሀገራት መካከል ምክክር እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም አህጉሪቱን የጦር መሳሪያ የማይሰማባት ማድረግ፣ ሽብርተኝነትን መዋጋት፣ አፍሪካዊ ውህደት መፍጠርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ውክልና ማሻሻል በአፍሪካ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ አታፍ በበኩላቸው ፥ አፍሪካ ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ውጥረትና መከፋፈልን ፈጥሮ ሚናዋን ከሚያደብዝዝባት ስርዓት የምትላቅቅበት የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ እንዲደረግ ትፈልጋለች ብለዋል፡፡

ኮሚቴውን በሊቀመንበርነት የሚመሩት የሴራሊዮን የውጭ ጉዳይ እና የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ቲሞቲ ሙሳ ካባ ፥ የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ለማድረግ አፍሪካዊ መግባባት ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑን በማመላከት የአፍሪካ መሪዎች ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የታቀደውን ምክክር እንዲያፋጥኑ ጠይቀዋል።

በፈረንጆቹ 2005 የተቋቋመው ኮሚቴው አልጄሪያ ፣ ኮንጎ ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ ፣ ኬንያ ፣ ሊቢያ ፣ ናሚቢያ ፣ ሴራሊዮን ፣ ሴኔጋል ፣ ኡጋንዳ እና ዛምቢያን እንደሚያጠቃልል የዘገበው ዥኑዋ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.