Fana: At a Speed of Life!

የተመዘገበው ስኬት የ7 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ ያመላክታል- ፍጹም (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አሥር ወራት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገበው ስኬት የ7 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ አመላካች መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻው የ100 ቀናት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ያለፉት 100 ቀናትን እና የሁለተኛው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ አፈጻጸም እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ሪፖርት አቅርበዋል።

በዚህም ባለፉት አሥር ወራት የ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ጠቁመው÷ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ14 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥት 425 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን እና ከዚህ ውስጥ 271 ቢሊየን ብሩ ከሀገር ውስጥ ገቢ የተሰበሰበ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

እንዲሁም ከሸቀጦች የወጪ ንግድ 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር፤ ከሬሚታንስ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን፤ የመንግሥት የበጀት ጉድለትም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ14 በመቶ መቀነሱን አብራርተዋል፡፡

ለ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች በሀገር ውስጥ እንዲሁም ከ300 ሺህ ለሚልቁ በውጭ ሀገራት የሥራ ዕድል መፈጠሩንም አንስተዋል፡፡

በአጠቃላይ በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች የተመዘገበው ስኬት ኢትዮጵያ የ7 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት እንደምታስመዘግብ አመላካች መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.