Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል በግድቡ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር ትናንትም ቀጥሎ ውሏል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር ትናንትም ቀጥሎ ውሏል።

የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ድርድሩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፥ በትናንትናው ስብሰባ ሶስቱ ሀገራት በህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እና ዓመታዊ የስራ ክንውን ጋር በተያያዘ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው መደራደራቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቅዋል።

በትናንትናው ውሎ ውይይት የተደረገባቸውም የመጀመሪያ የውሃ አሞላል ሂደት ህግና መመሪያዎች፣ ከድርቅ ጋር የተያያዙ የድርቅ ወቅት አስተዳደር፣ የግድቡ ደህንነት እና የግድቡ አካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖ ጥናት ናቸው።

በግድቡ ዙሪያ ሶስቱ ሀገራት እያደረጉት ያለው ድርድር ዛሬም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን፥ በዛሬው ውሎም ግድቡ ውሃ በሚይዝበት ወቅት እና ወደ ስራ ሲገባ ድርቅ ቢያጋጥም ምን አይነት የድርቅ ወቅት አስተዳደር ሊኖር ይገባል በሚለው ላይ ድርድሮች ይካሄዳሉ።

የድርቅ ወቅት አስተዳደርን በተመለከተ ኢትዮጵያ ግድቡ ውሃ ይዞ ወደ ስራ በሚገባበት ውቅት ድርቅ ካጋጠመ የሶስቱ ሀገራት የጋራ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል የሚል አቋሟን አንፀባርቃለች።

በውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ የሚካሄደው ድርድር ዛሬም በኢትዮጵያ ሊቀመንበርነት ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን፥ ከዚያ ቀደም ብሎ ግን የህግ ባለሙያዎች ቡድን በህግ ነክ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርግም ተገልጿል።

በሙለታ መንገሻ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.