Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሴቶችና ህፃናት የተቀናጀ እንክብካቤና ፍትህ ማዕከላትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን እና ህፃናትን ለመርዳት የተዘጋጁ የሴቶችና ህፃናት የተቀናጀ እንክብካቤና ፍትህ ማዕከላትን ጎበኙ።
 
በጋንዲ መታሰቢያን እና ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የሚገኙ የሴቶች እና ህፃናት የተቀናጀ እንክብካቤ እና ፍትህ ማዕከላት አግልግሎት አሰጣጥን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
 
በአሁኑ ወቅት የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች እና ህፃናት በህክምና ተቋማት የተለየ ክትትል ስለሚያስፈልጋቸው በሶስት ሆስፒታሎች በተለየ ሁኔታ ይህንን የማደራጀት ስራዎች መከናወናቸውም በጉብኝቱ ላይ ተገልጿል።
 
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፥ የሴቶች እና ህፃናት ጥቃትን ለመከላከል እና ጥቃት አድራሾች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
 
እስካሁን በተሰራው ስራም የሴቶች እና ህፃናት ጥቃትን የሚመለከቱ ችሎቶች በአፋጣኝ እንዲከፈቱ መደረጉን አስታውቅዋል።
 
በተጨማሪም በሴቶች እና ህፃናት ጥቃት የተጠረጠሩ 53 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ስራ መጀመሩንም ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል።
 
ከዚህ ቀደም ከሴቶች እና ህፃናት ጥቃት ጋር ተያይዘው ተከፍተው የነበሩ 23 መዝገቦች ወደ 29 ከፍ ማለታቸውን አስታውቀው፥ መርማሪ ፖሊስ መዝገቦችን በፍጥነት ወደ አቃቤ ህግ እንዲያስተላለፍ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
 
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የኢፌዲሪ የሴቶች እና ወጣቶች ሚኒስትር ድኤታ ወ/ሮ ስመኝ ውቤ በበኩላቸው የሴቶች እና ህፃናት ጥቃትን ለመከላከል የአንድ ማዕከል አግልግሎትን በማጠናከር እና በማስፋት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ሪፖርተራችን እንደዘገበችው ፍርድ ቤቶችም አፋጣኝ ፍርድ የመሥጠት ሂደትን ለማቀላጠፍ እየሠሩ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
 
 
በአክሱማዊት ገብረህይወት
 
#FBC
 
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.