Fana: At a Speed of Life!

የዓለም የኖቤል የሰላም ሎሬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም የኖቤል የሰላም ሎሬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ማለዳ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ በመሆን ሽልማታቸውን ከትናንት በስቲያ በኖርዌይ ኦስሎ በተካሄደ ስነ ስርዓት መቀበላቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ አዲስ አበባ ሲደርሱም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ለክብራቸውም 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።

በተጨማሪም በአውሮፕላን ማረፊያው የባህል ውዝዋዜ አቅራቢዎች እና የማርሽ ባንድ ለአቀባበሉ ድምቀት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሰላም እና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀው የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ተነሳሽነትን በመውሰዳቸው የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ኮሚቴው መግለፁ የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም ሁሉም ባለድርሻ አካለት በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ሰላም እና እርቅ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠትም እንደተመረጡ ኮሚቴው ገልጿል።

ኮሚቴው በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማምጣት ቃል መግባታቸውን በማስታወስ፥ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበል ሀገራቱ አስመራ ላይ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ ማስቻላቸውን ነው ያነሳው።

ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ስምምነት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻክሮ የነበረው የጅቡቲና ኤርትራ ግንኙነት እንዲስተካል ሚና እንደነበራቸው አስታውሷል።

በአልአዛር ታደለ እና በሀይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.