Fana: At a Speed of Life!

ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ሚድሮክ ኢትዮጵያን እንደገና በማደራጀት ሥራ አስፈጻሚዎችን ሾሙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚድሮክ ኢትዮጵያ ባለቤትና ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ሚድሮክ ኢትዮጵያን እንደገና በማደራጀት ሥራ አስፈፃሚዎችን መሾማቸው ተገለጸ።

ሹመቱን አስመልክቶ ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተደረገ ስብሰባ ምደባው ለኩባንያዎቹ ሥራ አስኪያጆች ተገልጿል፡፡

የኩባንያው ባለቤት ሼክ መሐመድ ላለፉት በርካታ ሳምንታት አዲስ መዋቅር ሲያስቡና ሲያስጠኑ ከቆዩ በኋላ ነው አዲሱን መዋቅር ዛሬ ይፋ ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዚሁ መሠረት ሚድሮክን በኢትዮጵያ ወክለው በዋና ሥራ አስፈፃሚነት እንዲያገለግሉ አቶ አብነት ገብረመስቀልን ሾመዋል፡፡

አቶ አብነት በኮንስክትራክሽን፣ በሆቴሎች እና በሪል ስቴት ዘርፍ ያሉትን ኩባንያዎች በተጨማሪ እንዲመሩ ተመድበዋል፡፡

እንዲሁም የመድኃኒት ፋብሪካቸውን ፋርማኪዩርን እየመሩ እንዲቀጥሉ ወስነዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ጀማል አህመድ በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ደረጃ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በንግድ፣ በግብርና እና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ያሉትን ኩባንያዎች እንዲመሩ ተሹመዋል፡፡

ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካን አቶ ኃይሌ አሰግዴ እየመሩ እንዲቀጥሉና ሌሎች ኩባንያዎችም በነበሩበት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችል አዲስ መዋቅር ይፋ መደረጉ ተገልጿል።

ባለሀብቱ ኩባንያዎቻቸው እንደወትሮው ለኢትዮጵያ እድገት በጥንካሬ መስራታቸውን እንዲቀጥሉ በዚሁ ወቅት መመሪያ መስጠታቸውም ተጠቁሟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.