Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል የከተሞች የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል የከተሞች የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዛሬ በጎንደር ከተማ ተጀምሯል።

በክልሉ በሚገኙ ከተሞች በክረምቱ ወራት 165 ሚሊየን ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን፥ ዛሬ በጎንደር ከተማ በተጀመረው የተከላ መርሐ ግብርም 20 ሺህ ችግኞች ተተክለዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይም የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ፋንታ ደጀን፥ የዘንድሮው የችግኝ ተከላ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች የሚተከሉ በመሆኑ ለወጣቶች ስራ ፈጠራና ለከተሞች ውበትም እንዲሆን ትኩረት በመሰጠቱን ያሳያል ብለዋል።

በአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ሰዒድ ኑሩ፥ “ዝናብ ሳናጣና ወንዞችም እያሉን ለድርቅ የምንጋለጠው አፈራችን እየተሸረሸረ በመሆኑ ችግኞችን በመትከል ይህንን ችግር ልንቀርፍ ይገባናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም በበኩላቸው፥ “ዛሬ የምንተክለው የነገ ታሪካችንን ነውና ሁሉም ዜጋ አሻራውን ሊያሳርፍ ይገባል” ብለዋል።

በተያያዘ ዜና በሰኔ 15ቱ ጥቃት ለተሰው የአማራ ክልል አመራሮች እና የፀጥታ አባላት መታሰቢያ የሚሆን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።

አረንጓዴ አሻራን ለማሳረፍ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ሂደት የአማራ ክልል የስራ ሀላፊዎችና የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር በሪሁን ካሳውን ጨምሮ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።

በተጨማሪም ከችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ጎን ለጎን ከዚህ በፊት የተነሳውን ጎርጎራን በጎንደር ከተማ ስር አድርጎ የማልማት ጥያቄ ለመመለስ ጉብኝት ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የጎርጎራ ከተማ ነዋሪዎች የልማትና የወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፥ ሃሳቡ ለክልሉ ምክር ቤት እንሚቀርብና በእቅድ እንዲካተት ትኩረት እንደሚሰጠው ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ሰዒድ ኑሩ ተናግረዋል።

በሙሉጌታ ደሴ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.