Fana: At a Speed of Life!

በሰበታና ጅማ ከተሞች ግንባታቸው የተጠናቀቁ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል በሰበታ እና ጅማ ከተሞች ግንባታቸው የተጠናቀቁ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ።
 
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ቀጣይነት ያለውን ልማት በማስቀደም እና ለክልሉ ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት በመስጠት 3 ሺህ 981 ግንባታቸው ለረጅም ጊዜ የተጓተቱ እና አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን 4 ነጥብ 81 ቢሊየን ብር በጀት መድቦ በማጠናቀቅ እያስመረቀ እንደሚገኝ የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
 
በዛሬው እለትም በሰበታ ከተማ በ563 ሚሊየን ብር በሆነ ወጪ የተገነቡ 76 የተለያዩ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል።
 
ግንባታቸው የተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶቹን በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ተመርቀዋል።
 
ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከልም የመማሪያ ክፍሎች፣ 23 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ ጌጠኛ ድንጋይ (ኮብል ስቶን) መንገዶች፣ የከተማ ፓርክ እና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።
 
በተመሳሳይ በጅማ ከተማም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በግንባታ ላይ የነበሩ 26 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በዛሬው እለት ተመርቀዋል።
 
ከ100 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡትን የልማት ፕሮጀክቶችም በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ የተመራ የክልሉ መንግስት ልኡካን መርቀዋቸዋል።
 
ግንባታቸው ተጠናቆ ከተመረቁ ፕሮጀክቶች ውስጥም ጌጠኛ ድንጋይ (ኮብል ስቶን) መንገዶች፣ የጠጠር መንገዶች የፍትህና የወረዳ ፍርድ ቤት ጽህፈት ቤቶች እና የመናፈሻ ስፋራዎች ይገኙበታል።
 
በተጨማሪም ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በክረምት በጎ ፍቃድ መርሃ ግብር በበጎ ፍቃደኞች የሚካሄድ በጅማ ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው 98 ሰዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታና እድሳትን መርሃ ግብርም አስጀምረዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.