Fana: At a Speed of Life!

ኬንያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለቀጠናዊ ውህደት አስፈላጊ መሆኑን ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኬንያ በኢትዮጵያውያን እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለቀጠናው የኢኮኖሚ ውህደት ጠቃሚ መሆኑን ገለጸች።

የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ  ጀስቲን ሙቱሪ ዛሬ በኬንያ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለምን በጽህፈት ቤታቸው ባነጋገሩበት ወቅት ÷ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ሊካሄድ የሚገባው ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን እንደሌሎች የአካባቢው ሀገሮች የተፈጥሮ ኃብታቸውን በመጠቀም የመልማት ተፈጥሮኣዊ መብት እንዳላቸው እንደሚገነዘቡም አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።

በወቅቱም አምባሳደር መለስ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል እየተካሄደ ስላለው የሶስትዮሽ ድርድር ገለፃ አድርገውላቸዋል።

በውይይቱም  በኢትዮጵያ እና ኬንያ ፓርላማዎች መካከል በተለያዩ ክፍለ-አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተደጋግፎ ለመስራት ከመግባባት  ላይ ደርሰዋል።

አምባሳደሩ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የግል ኑሯቸውን በድለው እየሰሩት ያለ መሆኑን አብራርተዋል

አምባሳደሩ አያይዘውም ጥቅሙ ግን ከአትዮጵያ አልፎ ለአካባቢው የሚተርፍ ፕሮጀክት መሆኑን እንደጀመሩት ለመጨረስ የማንንም ወገን ፈቃድ እና ችሮታ አይጠይቁም  ማለታቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ “የአፍሪካ መፍትሄዎች ለአፍሪካ ችግሮች” መርህ እንዲፈታ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

 

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.