Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ባሉ አንዳንድ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ባሉ አንዳንድ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዛሬው እለት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል።

በማሻሻያው መሰረት በተለያዩ ምክንያቶች ለሞት የሚዳረጉ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በማህበረሰቡ የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸም ተፈቅዷል።

ከዚህ ቀደም የአስክሬን የላቦራቶሪ ውጤት ከመምጣቱ በፊት የቀብር ሥነ ሥርዓት መፈጸም አይቻልም የሚለውን መመሪያ መሻሻሉን ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በቀብር ሥፍራ ላይ ከዚህ ቀደም የተቀመጠው 50 ሰዎች ብቻ ተገኝተው ሥርዓቱን ማካሄድ አለባቸው የሚለው መመሪያው አልተሻሻለም ብለዋል።

ግለሰቦች በኮሮናቫይረስ ቢያዙ የሚያገለግሏቸው የቤተሰብ አባላትና የራሳቸው ፍላጎት ከግምት በማስገባት ተፈጻሚ እንደሚሆንም ጠቅሰዋል።

የግሰለቦችን የአኗኗር ሁኔታ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት አግባብ ከሆነ በቤታቸው እንዲቆዩ እንደሚደረጉም ተገልጿል።

ከውጭ የሚገቡ ሰዎች በተለይም ወደ ሃገር ከገቡ በኋላ ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ ከመጡበት ሃገር ተመርምረው ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ ይዘው ከመጡ ናሙና ተወስዶ በቤታቸው 14 ቀናት እንዲቆዩ ይደረጋልም ተብሏል።

በሌላ በኩል ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋገጥ ሪፖርት ይዘው ለማይመጡ መንገደኞች ናሙናቸው ተወስዶ ለሰባት ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ይደረጋል ብለዋል ዶክተር ሊያ።

ይህም ከዚህ ቀደም ለ14 ቀናት የነበረውን አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ወደ ለ7 ቀናት ብቻ እንዲሆን መወሰኑን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.