Fana: At a Speed of Life!

የብልጽግና ፓርቲ የብሄር ማንነትና ሀገራዊ አንድነት ሚዛንን ለማስጠበቅ እንደሚያስችል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልጽግና ፓርቲ የብሄር ማንነትና ሀገራዊ አንድነት ሚዛንን ለማስጠበቅ እንደሚያስችል ተገልጿል።

“በህብር ወደ ብልጽግና”በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ አመራሮች በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና ህገ ደንብ ዙሪያ በ2ዙር ሲሰጥ የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ የስልጠና እና ውይይት መድረክ ተጠናቋል።

በውይይት መድረኩ ከከተማ ማዕከል እስከ ወረዳ አስተዳደር የሚገኙ ከ3 ሺህ 600 በላይ አመራሮች ተሳትፈዋል።

በዚህም የፓርቲው ውህደት ያለበት ደረጃ፣ በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና ህገ ደንብ እንዲሁም በፓርቲው ቀጣይ ወራት ዋና ዋና የድርጅትና የፖለቲካ ስራዎች አቅጣጫ ላይ ዝርዝር ውይይት መደረጉ ተገልጿል።

በማጠቃለያ መድረኩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በቡድን ውይይት ወቅት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል።

በምላሻቸውም የኢህአዴግ ግንባር ውህደት የተመራበት አግባብ ሳይንሳዊ በሆነ ጥናት፣ ሁሉን አሳታፊ እና የድርጅት እና የምርጫ ቦርድ የፓርቲዎች ምዝገባና የመተዳደሪያ ህገ ደንብ የተከተለ መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ከመገንባት አኳያ ውህደቱ ሁሉን አካታች መሆኑ እና የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳ ዘንድ አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት።

ብልጽግና ፓርቲ ህዝባዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነት፣ የህግ የበላይነት፣ ሀገራዊ አንድነትና ህብረ ብሄራዊነት መርሆችን የሚከተል መሆኑን ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በፕሮግራሙ ጠንካራና ተቀባይነት ያለው ዘላቂ መንግሥታዊ መዋቅርና ተቋማት መገንባት፣ የብሔር ማንነትና ሀገራዊ አንድነት ሚዛን የጠበቀ ማድረግ እንዲሁም አንድ ጠንካራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር አላማ እንዳለውም ተጠቁሟል።

ከዚህ ባለፈም ፓርቲው የህዝቦች ክብር፣ ፍትህና ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲሁም እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት የሚተገበርበት መሆኑን ነው ያብራሩት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.