Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል እየተነሱ ያሉ የመዋቅር ጥያቄዎች ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ተከትሎ ሊመለሱ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 13 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል እየተነሱ ያሉ የመዋቅር ጥያቄዎች ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ተከትሎ እንዲፈጸሙ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አሳስበ።

በደቡብ ክልል እየተነሱ ያሉ በክልል፤በዞንና በልዩ ወረዳነት በአዲስ መዋቅር የመደራጀት ጥያቄዎች የዴሞክራሲያዊ ሂደትን ተከትሎ በሠላማዊ፣ፍትሃዊና ለህዝቦች የጋራ አንድነት ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ምላሽ ለመስጠት መንግስት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታውቀዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ÷በተለይ ሲዳማ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ህዝቡ ያቀረበው ጥያቄ ህጋዊ መሰረት ይዞ ምላሽ እንዲያገኝ ያላሰለሰ ጥረት መደረጉን ገልፀዋል ።

አመራሮችም ሆኑ የህዝብ እንደራሴዎች  የራሳቸው ጥያቄ ከማስቀደም ይልቅ ሁሉንም ያካተተ ዘላቂ መፍትሔ ለማመቻቸት መረባረብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የሲዳማ ዞን በክልል ለመደራጀት የጠየቀው የመዋቅር ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝ የበለጠ ልማትን ለማሳለጥ እንጂ ልዩነት ለማምጣት አለመሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ከበፊቱ የበለጠ ትስስርን ለማጠናከር መሥራት ይጠበቅበታልም ነው ያሉት።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ሳኒ ረዲ በሰጡት አስተያየት÷ ክልሉ በነበረው ቆይታ የገነባው የህብረ ብሄራዊ ተምሳሌትነት አስደሳች እንደነበር አንስተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች እየተነሱ ያሉ የመዋቅር ጥያቄዎች ለመመለስ የፌዴራል መንግስት በሰከነና በዕውቀት ላይ ተመስርቶ እልባት እንዲያገኝ እየሰራ ያለው ተግባር የሚበረታታ ቢሆንም የክልሉ አመራሮች  ነፃ ሆነው ከማገዝ አንፃር ክፍተት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በተለይ በኮቪድ19 ምክንያት ሃገራዊ ምርጫ መራዘሙን ያስታወሱት አቶ ሳኒ ከዚያ አስቀድሞ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የመደራጀት ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊና በሰለጠነ መልኩ ሊፈቱ ይገባል ነው ያሉት።

ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ እልኩ ወንድማገኝ በበኩላቸው÷ በአዲስ መልክ ለመደራጀት እየተነሱ ያሉ ጥያቁዎች በክልሉ የነበረው የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ እጦትና ጉድለት የወለዳቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የመደራጀት ጥያቄው በዘላቂነት ምላሽ እንዲያገኝ መንግስት የተለያዩ ኮሚቴዎች በማደራጀት የጀመረውን ጥናት ፍጻሜ ላይ ማድረስ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የአደረጃጀት ጥያቄውን በሌላ መልኩ በመተርጎም በህዝቦች መካከል መቃቃርን የሚዘሩ ኃይሎች አጀንዳ ለማክሸፍ መንግስት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሊሰራ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.