Fana: At a Speed of Life!

“ዓላማችን የአዲስ አበባ ነዋሪ “ሰልፍን” ቢቻል ማቆም ቢያንስ ግን መቀነስ ነው”- ኢ/ር ታከለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዓላማ የአዲስ አበባ ነዋሪ “ሰልፍን” ቢቻል ማቆም ቢያንስ ግን መቀነስ ነው መሆኑን ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለፁ።

ምክትል ከንቲባው በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ይህ ወደ ኃላፊነት ከመጣንበት ቀን ጀምሮ ለራሳችን የገባነው ቃል ነው ብለዋል።

በትራንስፖርት ፣ ዘይትና ዳቦ በአዲስ አበባ ሰው ሳይጋፋ በቀላሉ ማግኘት አይታሰብም ያሉት ምክትል ከንቲባው ከሸማቾች ማህበራት የትኛውንም ምርት ለማግኘት ረጃጅም ሰልፎችን ማለፍ የመጀመሪያው የከተማዋ ነዋሪዎች የሚገጥማቸው ፈተና መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህም አልፎ በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት እድል ከቀና በአንድ ቀን የሚጠናቀቅ ካልቀናም ቀናትን የሚፈጅ ሰልፍን ማለፍ ግድ ይላል ሲሉ ነው የገለፁት።

የአገልግሎቶች መጓተት ነዋሪዎች ላይ ከሚያስከትለው አላስፈላጊ ውጣውረድ ባለፈም የከተማዋን ኢኮኖሚ በብርቱ የሚፈትን መሆኑን አንስተዋል።

በአገልግሎቶች ላይ የሚታዩ የጊዜ መጓተቶች የሰአት መባከኖች የሰዎችን ምርታማነት የሚቀንሱ በገንዘብ ሲተረጎሙም በኢኮኖሚው ላይ የሚታይ ጉዳትን የሚፈጥሩ ናቸው።

አዲስ አበባን የማስተዳደር ኃላፊነትን ስንረከብም ዋነኛ መነሻችን የሆነው የከተማዋን ነዋሪዎች ምርቶችን ያለሀሳብና ያለ ጊዜ ብክነት እንዲያገኙ አገልግሎቶችንም በማያማርር መልኩ እንዲያገኙ ማስቻል እንደሆነ ምክትል ከንቲባው ገልፀዋል።

ምክትል ከንቲባው መነሻ ጥቅል ሀሳባችንም የከተማዋን ነዋሪዎች “ሰልፍ” ቢቻል ማቆም ቢያንስ መቀነስ የሚል ነው! ይህ መነሻ ሀሳባችን በአንድ በኩል የከተማችንን ነዋሪዎች የኑሮ ደረጃና የሚያገኙትን አገልግሎቶች በማሻሻል የነዋሪዎች የኑሮ ሂደት ላይ ልዩነት መፍጠር በሌላ መልኩ ደግሞ በጊዜ ብክነት እያጣነው ያለውን እልፍ ገንዘብ ማዳን ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

እነዚህን ቁልፍ የሆኑ ከከተማዋ ነዋሪዎች የእለት ተእለት ህይወት ጋር ቀጥታ ግኑኝነት ላላቸው ችግሮች ዛሬን የሚያሻግር መጪ ፍላጎትንም በብቃት መቋቋም የሚችል መፍትሄ ማምጣትም የአስተዳደራችን ዋነኛ ትኩረት እንዲሆን አድርጓል።

ህብረተሰቡ በቅርብ የሚያገኛቸው አብዛኛው አገልግሎቶች የሚሰጥባቸው የወረዳ ጽህፈት ቤቶች አሰራራቸው የተፋጠነ እንዲሆን በተለይ አብዛኛው ሰዓት የሚፈጀው የግለሰቦችንም የተቋማት መረጃን መፈለግ እንዲቃለል ከአስተዳደደሩ ዋና ጽህፈት ቤት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ድረገጽና የመረጃ ቋት እንዲበለጽግ መደረጉን አስታውቀዋል።

ይህም የነዋሪዎች የጥበቃ ሰዓትን በማሳጠር የተፋጠነ አገልግሎት እንዲያገኙ ትልቁን አበርክቶ ተወጥቷል ነው ያሉት፡፡

በትራንስፖርት ፣ ዘይትና ዳቦ የሚታዩትን ሰልፎች ለመቅረፍም ግንባታው የተጠናቀቀው የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ፣ እየተገነባ ያለው የዘይት ፋብሪካ እና አዲስ አበባን በብርቱ የሚፈትነውን የትራንስፖርት ዘርፉን ለማሻሻል እየተከናወኑ የሚገኙት በርካታ ስራዎች አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.