Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የሥነ-ህንፃና የሥነ -ከተማ ዲዛይን ማዕከል ተከፈተ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ የሥነ-ህንፃ እና የሥነ -ከተማ ዲዛይን ማዕከል ዛሬ በይፋ በከተማዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተከፈተ።
 
በመስቀል አደባባይ አካባቢ የተከፈተው ይህ ማዕከል በከተማዋ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች እና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን የሚያስቃኝ የፎቶግራፍ እና ሌሎች የስና እንፃ ማሳያ የሆኑ ምስሎች የሚገኙበት ነው።
 
ኢንጂነር ታከለ የአዲስ አበባን የከተማነት ጉዞ አበይት መልኮች እና የወደፊት ዕይታችንን ሻይ ቡና እያልን በእውቀት የምንመለከትበት እና የምንመካከርበት ትልቅ የሥነ-ህንፃ እና የሥነ -ከተማ ዲዛይን ማዕከል እንደሚሆን ነው ከዚህ በፊት የገለፁት።
 
በማእከሉ የትኛውም ዜጋ ስለከተማዋ እቅዶችና ፕሮጀክቶች መመልከትና የራሱን ሀሳብ በፅሁፍና በድምፅ መስጠት እንደሚችል የከንቲባ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
 
የተሰጡት አስተያየቶች በቦታው የሚገኙ ባለሙያዎች በማሰባሰብ ለከንቲባው በየጊዜው የሚያቀርቡ ይሆናል።
 
የማእከሉ መቋቋም የከተማዋ ነዋሪ በከተማዋ ላይ ያለው ተሳትፎ እንዲጨምርና ስለ ከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ላይ ግንዛቤ እንዲፈጠርና ግልፅነት ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል።
በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የመዲናይቱን ገፅታ ፍፁም የሚቀይሩ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑባት ትገኛለች።
 
በቢሊየን የሚቆጠር ብር ወጪ ከተደረገባቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀከት አካል የሆኑት የወንዞች ዳርቻ ልማት እና የአንጦጦ ፓርክ ግንባታ ይገኙበታል።
 
በተጨማሪም የአድዋ ፓርክ፣ የቤተ መፅሃፍት ግንባታና የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክቶችም ተጠቃሾች ናቸው።
 
በለይኩን ዓለም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.