Fana: At a Speed of Life!

አገር አቀፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ሰኔ 16 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሃገሪቱ 10 ነጥብ 1 ሚሊየን ወጣቶችን ተሳታፊ የሚያደርገው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዛሬ መጀመሩን የኢፌዲሪ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጀት ዓመቱ ሃገር አቀፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በደብረ ብርሃን ከተማ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በችግኝ ተከላ መጀመሩ ተገልጿል።

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ሃይሉ ÷ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ወጣቶች የሚሳተፉበት 10 የስራ ዘርፎች መለየታቸውን ተናግረዋል።

በተለይ በዚህ የክረምት ወቅት በአካባቢ ጥበቃ ስራ በመሳተፍ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ከደለል ለመታደግና የጣናን እምቦጭ ለመንቀል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

በተያያዘም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመከላከል በበጋው ወቅት የተጀመሩ ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ከዚያም ባለፈ ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎት፣ የደን ልማት፣ ደም ልገሳ፣ የእርሻ ስራና መሰል ተግባራት በተደራጀ አግባብ የሚቀጥሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በወጣቶቹ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም 23 ሚሊየን ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል።

ኮቪድ-19 ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮም ሁለት ሚሊዮን ወጣቶችን በመሳተፍ ለ49 ሚሊየን ዜጎች ትምህርት በመስጠት፣ እጅ በማስታጠብ፣ ማዕድ በማጋራት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የክረምት ወቅት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስኬታማ እንዲሆንም በየደረጃው ያለው አመራር ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግም ሚኒስትር ዴኤታዋ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.