Fana: At a Speed of Life!

ኪም ጆንግ ኡን በደቡብ ኮሪያ ላይ ሊወስዱት የነበረውን ወታደራዊ እርምጃ አገዱ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሰሜን ኮሪያ በጎረቤት ደቡብ ኮሪያ ላይ ልትወስድ የነበረውን ወታደራዊ እርምጃ ማገዷን አስታወቀች።

የገዥው ፓርቲ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮሚሽን በቪዲዮ ኮንፈረስ የታገዘ ውይይት ካደረገ በኋላ ፒዮንግያንግ አስባው የነበረውን ወታደራዊ እርምጃ ማቋረጧን አስታውቋል።

በቅርብ ሳምንታት ሁለቱ ሃገራት በሚዋሰኑት ድንበር ፀረ ሰሜን ኮሪያ ይዘት ያላቸው ፅሁፎች በስፋት ሲሰራጩ ነበር።

ፒዮንግያንግም ድርጊቱ ሃገራቱ የገቡትን ስምምነት የጣሰና ብሄራዊ ክብርን የሚነካ ነው በማለት ኮንናዋለች።

ለደቡብ ኮሪያዎች ምላሽ ለመስጠትም በድንበር አካባቢ ፀረ ደቡብ ኮሪያ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች የሚያስተላልፉ የድምጽ ማጉያዎችን ተክላም ቆይታለች።

ይህን ተከትሎም ሁለቱ ሃገራት ከረር ያለ ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ቆይተዋል።

በተጨማሪም ፒዮንግያንግ በደቡብ ኮሪያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል እቅዷን ነድፋ ስትንቀሳቀስ መቆየቷን መረጃዎች ያመላክታሉ።

አሁን ላይም ማዕከላዊ ኮሚሽኑ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከእርምጃ መታቀቡን ገልጿል።

ከዚህ ባለፈም በድንበር አቅራቢያ የተተከሉ የፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ ድምጽ ማጉያዎችን ለማንሳት ተስማምታለች።

ምንጭ፡- አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.