Fana: At a Speed of Life!

እንደ ሃገር የምንፈተንበት እንደ ዜጋ የምንመዘንበት ወቅት አሁን ነው – ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ሰኔ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እንደ ሃገር የምንፈተንበት እንደ ዜጋ የምንመዘንበት ወቅት አሁን መሆኑን በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እና ሙያተኞች ገለፁ።

እኛ በኢትዮጵያውያን ለዘላቂ ለውጥ በሚል መጠሪያ የተሰባሰቡት በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እና ሙያተኞች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ተስፋና ፈተናዎች ዙሪያ የቪዲዮ ውይይት አድርገዋል።

በዚህ ወቅት የኮሮና ወረርሽኝ በህይወትና በማህበራዊ ኑሮ እንዲሁም በምጣኔ ኃብት ላይ በኢትዮጵያ በሚያደርሰው ጫና ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በተለይ ዓለም አቀፉዊ የምጣኔ ኃብት ቀውስ በኢትዮጵያ የእድገትና የብልፅግና ትልም ላይ የሚፈጥረው ጫና እንዲሁም ከምርጫው ጊዜ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎች ዙሪያም ምክክር እንደተካሄደም ነው የተነገረው።

በዋነኝነት ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ በሃገሪቱ ላይ ሊኖር ስለሚችለው ወታደራዊ ትንኮሳን ከግንዛቤ በማስገባት ጊዜው ከግልና ከቡድን ጥቅም በላይ አንድነት መናበብን የሚጠይቅ ነው ተብሏል።

በወይይቱ በአሁኑ ወቅት ዜጎች የሃገሪቱን ህግ በማክበር፣ የሙያተኞች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና የሃገር ሽማግሌዎችን ምክር እና ሀሳብ በማዳመጥ የቤተሰብና የአካባቢን ሰላም ጤና ደህንነት መጠበቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑም ተጠቁሟል።

ከዚህ ውጭ በመቆም ሁኔታውን ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም ለመጠቀም የሚሞክሩ ወገኖች የሚገጥማቸውን ውርደትና ውድቀት ሊያጤኑት ይገባል ብለዋል ምሁራኑ።

ከቅርቡ የሃገራችን ታሪክ እንደምንማረው ሃገር አደጋ ላይ ስትወድቅ ከጠላት ጋር የቆሙ በቀጥታም ይሁን የሀገሪቷን ደህንነት በተዘዋዋሪ ለድርድር ያቀረቡ ተዋርደዋል ወድቀዋል ሲሉም ገልጸዋል።

በመሆኑም ወቅቱ ሀገራችን እንደታላቅ ሃገር የምትፈተንበት እኛም ደግሞ እንደ ዜጋም ሆነ እንደ ልሂቅ የምንመዘንበት ወቅት ላይ ነንና በአንድነት በታላቅ የወገን ክብርና በሃገር ፍቅር ስሜት አብረን እንድንቆም በጥብቅ እናሳስባለን በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.