Fana: At a Speed of Life!

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርቡ በሱዳን የወጣው ሕግ ኢትዮጵያውያንን የማይመለከትና እየተካሄደ ያለው እስር እንደሚቆም ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን በቅርቡ የወጣው ሕግ ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት እንዳልሆነ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ጋር በመነጋጋር እስሩ እንደሚቆም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ አስታወቁ፡፡

በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምሳደር ሽፈራው ጃርሶ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብደላ ሐምዶክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚህ አምባሳደሩ በቅርቡ የሱዳን መንግስት ያወጣውን የውጭ ዜጎች በተለያዩ የንግድ ስራዎች እንዳይሰማሩ የሚያግደውን ሕግ አፈጻጸም ተከትሎ አፈሳና እስርን ጨምሮ በዜጎቻችን ላይ የተለያዩ እንግልቶች እየደረሱባቸው መሆኑን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

መንግስት በኢትዮጵያና ሱዳን መካካል ያለውን የወንድማማች ግንኙነት እንዲሁም ለዘመናት የዘለቀውን ታሪካዊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ስራዎችን እንዲያከናውም ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ቡጣቃና የመኖሪያ ፈቃድ ባላቸው ዜጎች ላይ ጭምር የሚጣለው ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ጁኔህ የሚደርስ የተጋነነ ቅጣትና በፍርድ ቤቶች አካባቢ ያለተገቢ ማጣራት በቅጽበት የሚሰጡ ፍርዶችን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ለሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ባለስልጣናት ማሳወቃቸውን አንስተዋል።

አያይዘውም እነዚህን ጉዳዮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትኩረት እንዲያዩት እና እልባት እንዲሰጡም ነው የጠየቁት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክም በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካካል ያለውን ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አውስተው በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለሃገሪቱ ኦኮኖሚ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል።

እንዲሁም በቅርቡ የወጣው ሕግ ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት እንዳልሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር፥ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ጋር በመነጋጋር አፈሳው እንዲቆም ይደረጋል ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም በፍርድ ቤቶችና በጸጥታ አካላት የሚደርሱ ጥፋቶችን አስመልክቶ ሪፓርት እንዲቀርብላቸው መመሪያ ማስተላለፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም ጉዳዩ በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት እንደሚያገኝ ማረጋጋጫ ሰጥተዋል።

በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ሽፈራው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የላኩላቸውን መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.