Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን አቋም በማስረዳት ረገድ የሀይማኖት ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን አቋም በማስረዳት ረገድ የሀይማኖት ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

ተቋማቱ ለግብጽም ይሁን ሌሎች ዓለም አቀፍ አቻ ተቋማት የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የመጠቀም መብትና አቋም በማስረዳት ዲፕሎማሲያዊ ስራን መስራት እንደሚችሉ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የሃይማኖት መሪዎች ተናግረዋል።

እውነት አለኝ ካለችው ሀገር ኢትዮጵያ ይልቅ ሃሰትን በድግግሞሽ እውነት ያስመሰለችው ግብጽ የሌሎችን መረዳት በመለወጥ ረገድ የተሳካላት ሆኖ ይነሳል።

ያነጋገርናቸው የሀይማኖት መሪዎችም የአማንያን የሆነች ሀገር ባላት የተቋማት ግንኙነት ሰፊ ሚና ባላቸው የሀይማኖት ተቋሞቿ አቋሟን ለማስረዳት መንቀሳቀስ አለባት ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የበላይ ሃላፊ ብጹዕ አቡነ አረጋዊ እንደሚሉት ጉዳዩ አጀንዳ ሆኖ የሚቀርብባቸው አጋጣሚዎች በመኖራቸው ማስረዳቱ እጅጉን ጠቃሚ ነዉ።

በኦሮርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ግብጽ እና ኢትዮጵያ ረጅም አመታትን ያስቆጠረ ትስስር እንዳላቸው ጠቅሰው ይህን ግንኙነት በመጠቀም ፍትህ ላይ የቆመውን የኢትዮጵያን አቋም ለማስረዳት መስራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የሀይማኖት መምህሩ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ ደግሞ ግብጽ የሃይማኖት መልክ ልትሰጠው ያሰበችውን የፍትህና የመብት ጥያቄ በእስላማዊ ተቋማት በኩል ለግብጽም ይሁን ዓለም አቀፍ ተቋማት በአቋም መግለጫ ጭምር ማድረስ አስፈላጊ መሆኑን አንስቷል።

ኡስታዝ አቡበክር የኢትዮጵያ ኡለማዎች ምክር ቤት ለዓለም ለግብጽ ኡለማዎች ምክር ቤት የኢትዮጵያን አቋም የሚያስረዳ ደብዳቤ በመጻፍ እና የልኡክ ቡድን በመላክ ጉዳዩን ማስረዳት እንደሚኖርበትም አስረድቷል።

ተቋማትን በዚህ ወሳኝ ጊዜ መጠቀም እጅጉን አስፈላጊ ነው የሚለው ኡስታዝ አቡበክር ሁለቱ ህዝቦች ካላቸው የሃይማኖት ትስስር አንጻር ከፖለቲካዊው ዲፕሎማሲ ባልተናነሰ ተጽእኖ መፍጠር ይችላሉ ብሎ እንደሚያምንም ይገልጻል።

እናም የኢትዮጵያ አቋም ለማንም መገለጥ ያለበት ሀቅ በመሆኑና የሁሉም ወገን ጥቅም መሆኑን በሚያረጋግጥ መንገድ ለተቋማት ማድረስ አስፈላጊ ስለመሆኑም አውስቷል።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዚዳንት ዶክተር እያሱ ኤልያስ በበኩላቸው ጉዳዩን ማስረዳት የእምነት ተቋማትን ብቻ ሳይሆን የተከታዮቻቸውንና አቅሙ ያላቸውን ሚና የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

በሀብታሙ ተክለስላሴ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.