Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ክልላዊ ምርጫ ለማድረግ ያቀረበውን ጥያቄ እንደማይቀበል አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ክልላዊ ምርጫ ለማድረግ ያቀረበውን ጥያቄ እንደማይቀበል አስታወቀ፡፡

ቦርድ ለጣቢያችን በላከው መግለጫ የትግራይ ክልል ምክር ቤት “ኮቪድ 19ኝን እየተከላከለ 6ኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ የወሰነ በመሆኑ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሚያዘው መሰረት ቦርዱ ውሳኔውን ተቀብሎ ምርጫውን እንዲያስፈፅም፣ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልግ የሰው ሃይልና ሎጂስቲክስ ዝግጅት እንዲያደርግ እና ውሳኔውን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቀን” ሲል ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር አስታውሷል፡፡

6ኛው ሃገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ እንዲራዘም ምክንያት የሆነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሁኔታ እንደገና ተገምግሞ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ እስከረጋገጥ ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል ምርጫ አያካሂድም ብሏል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠር እና ማስተዳደር፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣ የምርጫውን ከተጽእኖ ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማስፈጸም ስልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም መሆኑንም አንስቷል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳን፣ አፈጻጸምንም ሆነ ተያያዥ ሁኔታን የሚወስነውም ቦርዱ ብቻ በመሆኑም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ 6ተኛውን ዙር የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም ቦርዱ ይህንን ውሳኔውን ተቀብሎ ሊያስፈጽም ይገባል የሚልበት ህጋዊ መሠረት የለውምም ነው ያለው።

በመሆኑም ቦርዱ ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የትግራይ ክልል ምክር ቤት የክልል ምክር ቤት ምርጫን አስመልክቶ የሰጠውን ውሳኔ እንዲያውቅለትም ሆነ ምርጫ እንዲያስፈፅምለት ያቀረበውን ጥያቄ ያልተቀበለው መሆኑን በመግለጽ የተጠየቀውን የሰው ሀይል፣ የሎጂስቲክስ እና የቁሳቁስ አቅርቦት የሚሰጥበት የህግ አግባብ አለመኖሩን አስታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ምርጫውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የህዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ባለበት ሁኔታ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ የፌደራልና ክልል ምክርቤቶች የስልጣን ዘመን እንዲቀጥል እንዲሁም አጠቃላይ ምርጫው ስልጣን ያላቸው አካላት ወረርሽኙ የህዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበት ጀምሮ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ አመት ባለው ጊዜ እንዲካሄድ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.