Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል የአስፈጻሚ ተቋማት ግምገማ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 18 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል የአስፈጻሚ ተቋማት የ2012 በጀት ዓመት ማጠቃለያ የስራ ክንውን ግምገማ ተጀመረ ።

የክልሉ መንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸውን ተግባራት እንደሚገመግሙ ተገልጿል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ÷በክልሉ ለውጡን ተከትሎ የተፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት የህዝብን ደህንነትና ሠላም ለማረጋገጥ መንግሥት የወሰዳቸው እርምጃዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።

ከአደረጃጀት፣ መልካም አስተዳደርና ልማት ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ ተፈጥሮ የነበረው የተዛባ አመለካከትና አለመተማመን ህዝብን በማዳመጥ ለመመለስ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም አንስተዋል።

አቶ ርስቱ አያይዘውም ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉንና የጸጥታ ችግር ከምንጩ ለማድረቅ የተከናወኑ ስራዎች መልካም እንደነበሩ  አስረድተዋል።

በተለይ የህዝብ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በተደረገው ጥረት የዘገዩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ መመቻቸታቸውንም አስታውቀዋል።

መንግሥት የህዝብን እርካታ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ የፈጠረው ችግር ፈታኝ እንደነበር ጠቅሰው ÷”ስርጭቱን ለመቆጣጠር ህዝብና መንግሥት ርብርብ እያደረጉ ነው ” ብለዋል።

የክልሉ መንግስት አስፈጻሚ ተቋማት የበጀት ዓመቱ የስራ ክንውን ግምገማ ዓላማ የነበሩ መልካም ተሞክሮዎችን ለማስቀጠልና ክፍተቶችን በማረም በቀጣዩ ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲመቻቹ ለማስቻል  መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.