Fana: At a Speed of Life!

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘላቂ እንዲሆን በመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ሊደገፍ እንደሚገባ የዘርፉ ተመራማሪዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘላቂ እንዲሆን በመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ሊደገፍ እንደሚገባ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የደን ልማት ተመራማሪዎች ተናገሩ።

የአካባቢ ጥበቃ እና ልማት ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር በላይ ስማኔ እና የደን ልማት ተመራማሪ ዶክተር ውባለም ታደስ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለአረንጓዴ አሻራ ልዩ ትኩረት መስጠታቸው ለዘርፉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና ልማት ተመራማሪ ፕሮፌሰር በላይ ስማኔ፥ የዘንድሮው አካሄድ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ነገር ይታይበታል ብለዋል።

ከ20 ዓመታት በላይ በደን ልማት ዘርፍ ላይ ጥናት እና ምርምር እያካሄዱ የሚገኙት ዶክተር ውባለም ታደሰም፥ ከባለፉት ዓመታት የተለየ የሚያደርገው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ቁርጠኝነትና ለዘርፉ የሰጡት ልዩ ትኩረት ነው ይላሉ።

ተስፋ የተጣለበት የአረንጓዴ አሸራ ታላሚውን ግብ እንዲያሳካ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተመራማሪዎቹ አክለው አንስተዋል።

ተመራማሪዎቹ አክለውም በየዓመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም እና በየ በጋ ወቅት የሚካሄደው የተፋሰስ ልማት መርሃ ግብር ዙርያ አንድ የሚታይ ክፍተት አለ ይላሉ።

ዶክተር ውባለም፥ እነዚህ መርሃ ግብሮች በጥናት እና ምርምር መታገዝ ይጎላቸዋል ሲሉ ይናገራሉ።

እርሳቸው እነዚህ እጅግ ጠቃሚ ስራዎች የትኩረት አቅጣጫቸውም የተራቆተ መሬት ከመሸፈን አልፎም  የውህ መነሻ ወደ ሆኑ ተራራዎች አካባቢም ሊያተኩሩ ይገባል ነው የሚሉት።

ተፈጥሮ የሰጠንን የውሃ ሀብት በራሳችን ድክመት ለአደጋ እያጋለጥነው መሆኑን ይናገራሉ።

ተመራመሪው እንደሚሉት በወንዞች እና ሃይቆቻችን አካባቢ የተፋሰስ ስራ አለመስራታችን ታላላቅ ሃይቆቻችን አደጋ ውስጥ እንዲወድቁ  አድርጓል ባይ ናቸው፤ ለዚህም ታላቁን ጣና በማሳያነት ያቀርባሉ።

ፕሮፌሰር በላይ ስማኔም በዚህ ሀሳብ የሚስማሙ ሲሆን፥ የአረንጓዴ አሸራ ልማትን በእነዚህ አካባቢ ተግባራዊ ማድረግ የችግሩ አንድ መቀልብሻ እንደሆነ ያምናሉ።

ምሁራኑ ከአረንጓዴ አሸራ ጎን ለጎንም ያሉንን ሀብቶችም መጠበቅ መጠናከር አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

በስላባት ማናዬ

 

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.